ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

የመጨረሻው ፅሁፋችን ደግሞ በዚህኛው ሳምንት ያስተዋልናቸው ሌሎች ትኩረት የሚስቡ ጉዳዮች የቀረቡበት ነው።

👉 የተሳታፊ ክለቦች ቁጥር ይጨመር ይሆን ?

ካለፉት ጥቂት ቀናት አንስቶ በሊጉ ከቀጣይ ዓመት አንስቶ የተሳታፊ ክለቦች ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚለው ጉዳይ በስፋት በእግርኳሱ ዙርያ ባሉ አካላት መካከል እየተንሸራሸረ ይገኛል።

ከዚህ ጋርም በተያያዘ ከሊጉ መውረዱን ያረጋገጠው የሰበታ ከተማው አሰልጣኝ ብርሃኑ ደበሌም ከባህር ዳር ጋር አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ስለዚህ ጉዳይ ጥቂት ነገር ብለዋል ፤ “መረጃው የለንም። ጭምጭምታ ነው፡፡ በሁሉም ዘንድ የሚነገር ነገር ስለሆነ በዕርግጠኝነት በይፋ የወጣ ስላልሆነ……” የሚል እና በገደምዳሜ ይህን ሀሳብ በተለይ በወረዱ እንዲሁም ለመውረድ በቋፍ ላይ በሚገኙ ክለቦች አካባቢ በስፋት እየተንሸራሸረ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።

እርግጥ በሀሳቡ ዙርያ በይፋ ከሚመለከተው አካል የተባለ ነገር ባይኖርም አሁን ባለን የእግርኳሳዊ ደረጃ የሊጉን ተሳታፊ ክለቦች ቁጥር አሁን ላይ ካለው በላይ መጨመር ለውድድሩ የጨዋታ ብዛት ከመጨመር ባለፈ የሚጨምረው አንዳች ነገር ይኖራል ብሎ ማሰብ ስህተት ይመስላል።

የእግር ኳሳችን ሁለንተናዊ ዕድገት ማለትም ከአጠቃላይ የክለቦች ቁመና ፣ መሰረተ ልማት ፣ የተጫዋቾች ጥራት እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ አምርታን ለማምጣት በቂ ሥራ ባልተሰራበት በዘፈቀደ የክለቦች ቁጥርን ማብዛት ለእግርኳሱ እምብዛም ትርጉም አይኖረውም። ይልቁኑ ሌሎች እግርኳሳቸውን ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየሰሩ የሚገኙ ሀገራት እንዳደረጉት የሊጉ ተሳታፊ ክለቦችን ቁጥር ከነባራዊ ሁኔታ አንፃር በመመጠን የተሻለ እና ተፎካካሪ ሊግን መፍጠር ትክክለኛው አማራጭ ይመስላል።

በድፍረት ያለ በቂ ጥናት የተጣደፉ እና የሀገሪቱን እግርኳስ የሚወስኑ ጉዳዮች ላይ በግብታዊነት ውሳኔዎችን ማሳለፍ የተለመደ በሆነበት እግር ኳሳችን ምናልባት አንድ ቀን ከእንቅልፋችን ስንነሳ የሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ቁጥሮች ይህን ያህል ሆኗል የሚለውን ዜና ብንሰማ ብዙ የሚያስገርም አይሆንም። በመሆኑም ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምናልባት ከመጋረጃ በስተጀርባ ሥራዎች እየተሰሩበት ሊሆን ይችላል ብሎ መጠርጠሩ አዋጩ አማራጭ ይመስላል።

👉 የባህር ዳር ደጋፊዎች አሁንም ማስገራማቸውን ቀጥለዋል

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት “ዘንባባዎች” በተለየ ድምቀት እና ህብር በ”በላይ ዘለቀ” ደምቀው ተመልከተናቸዋል።

ባህር ዳር ከተማ ከሰበታ ከተማ ጋር ካደረጉት ጨዋታ መጀመር አስቀድሞ የክለቡ ደጋፊዎች የባህር ዳር ስታዲየምን የተለየ ድባብ ለማላበስ ከፍተኛ ርብርብ ሲያደርጉ ያስተዋልን ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ “በባለሜዳነት” ባደረገው የመጨረሻ ጨዋታ በባህር ዳር ስታዲየም የተመልካቾች መቀመጫ ክፍል ስያሜ መሰረት ከክብር እንግዶች መቀመጫ ፊት ለፊት በሚገኘው “በላይ ዘለቀ” የመቀመጫ ክፍል የተለየ ድባብን ተመልክተናል።

በዚሁ ክፍል በሚገኘው ሁለተኛው ወለል ላይ የክለቡ መለያ ቀለሞች የሆኑት ነጭ እና ውሃ ሰማያዊ ቀለማት የተሰሩ ረጃጅም ጨርቆች ተወጥረው የተመለከትን ሲሆን በታችኛው የመቀመጫ ክፍል ደግሞ ለወትሮው ያለ መለያ የማይገባበት “የዘንባባ” የመቀመጫ ክፍል ተመልካቾች ከነአስገራሚ ህብረ ቀለማቸው ወደ “በላይ ዘለቀ” የመቀመጫ ክፍል አምርተው የተመለከትናቸው ሲሆን በዚህም በሞዛይክ የተደገፈ እጅግ አስደናቂ ድባብን እንዲሁ አስመልክተውናል። የሊጉን የመጨረሻ ሳምንታት የተለየ ቀለም እያላበሱ የሚገኙት የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች እርግጥ የቡድናቸው የሜዳ ላይ ውጤት ብዙም የሚያስደስት ባይሆንም አሁንም ቢሆን ቡድናቸውን ውጤታማ ለማድረግ አስገራሚ ድጋፋቸውን እየለገሱ ይገኛል።

ከዚህ ባለፈ እንዲሁ ፋሲል ከነማም ኢትዮጵያ ቡናን በገጠመበት ጨዋታም የዐፄዎቹ ደጋፊዎች በተመሳሳይ በስታዲየሙ በቁጥር በርከት ብለው በመታደም አስደናቂ ድባብን ያስመለከቱን ሲሆን በተመሳሳይ ምንም እንኳን በቁጥር አነስ ይበሉ እንጂ ብዙ ኪሎሜትሮችን አቋርጠው ባህር ዳር የተገኙት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችም እንዲሁ ቡድናቸው በዝናብ ውስጥ ሆነው ሲያበረታቱበት የነበረበት መንገድ እውቅና የሚገባው ነበር።

👉 ስህተት የተሞላበት ስሞችን የማሳጠር ሂደት

በሊጉ በተለይ ከተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አንስቶ በመለያዎች ላይ የተጫዋቾች ስምን ማስፈር እየተለመደ መጥቷል።

ታድያ በዚህ ስሞችን የማስፈር ሂደት ውስጥ በርከት ያሉ ጥቃቅን የሚመስሉ ነገርግን የሊጉ ገፅታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያላቸውን ጉዳዮችን እያስተዋልን እንገኛለን። ከእነዚህ መካከል በብዙ መለያዎች ላይ እያስተዋልነው የምንገኘው ህፀፅ ስሞችን በማሳጠር ሂደት የሚፈፀም ስህተት ነው። ከመለያዎች በስተጀርባ በሚኖረው የስሞች መፃፍያ ቦታዎች ላይ አንዳንድ መለያዎች ላይ የተጫዋቾች ስም ብቻ ሰፍሮ ያስተዋልን ሲሆን በአንዳንዶቹ ላይ ግን የተጫዋቾቹ ስም በሙሉ እንዲሁም የአባታቸው ስም የመጀመሪያ ፊደል ተፅፎ ይስተዋላል። ታድያ ስህተቶች የሚጎሉት ሁለተኛውን አማራጭ ጥቅም ላይ በዋለባቸው መለያዎች ላይ ነው። በዚህ መንገድ ስሞችን ለመፃፍ በሚደረገው ሂደት የተጫዋቹን የአባት ስምን አጥሮ መፃፉን ለማመልከት የምትገባዋ ነጥብ (.) ያለቦታዋ በተጫዋቾቹ ስም እና በአባት ስም የመጀመሪያ ፊደል መካከል ስትቀመጥ እያስተዋልን እንገኛለን።

በእንግሊዝኛ ቋንቋ ስሞች ለማሳጠር መደበኛ በሆነው መንገድ ቀድሞ የሚፃፈው ስም የመጀመሪያ ሆሄ ቀጥሎ ነጥብ ከዚያ ቀጣዩ ስም በሙሉ ዘርዝር መፃፍ (A. ABCD) አሊያም ኢመደበኛ በሆነ መንገድ ደግሞ የመጀመሪያው ስም ሙሉውን ተዘርዝሮ ከተፃፈ በኋላ ቀጥሎ ከሚመጣው ስም የመጀመሪያ ሆሄ ከዚያ ነጥብ ማስቀመጥ (ABCD A.) ሁለት አማራጮች ሆነው ሳለ በሀገራችን አብዛኛዎቹ መለያዎች ላይ ነጥቧ በሁለቱ ስሞች መካከል (ABCD.A) በሚለው በተሳሳተ መንገድ የታተሙ መለያዎችን እየተመለከትን የምንገኝ ሲሆን ይህም በተለይ በቀጣዩ ዓመት መታረም ይገባዋል።

👉 የባህር ዳር ስታዲየም ተፈትኗል

በሀገራችን ደረጃ በብዙ መመዘኛዎች የተሻለ የሆነው የባህር ዳር ስታዲየሞ ባለፉት ሁለት ቀናት በአካባቢው የጣለው ዝናብ ግን ስታዲየሙን ለጨዋታ ፈታኝ አድርጎት ተመልክተናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአርባምንጭ እንዲሁም አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ያደረጓቸው ጨዋታዎች በተለይ ሁለተኛ አጋማሽ ክፍለ ጊዜያቸው በከፍተኛ ዝናብ ታጅበው የተደረጉ ነበሩ። በዚህ ሂደት በግቡ ትይዩ በተለይም መሀል ሜዳው እና ሁለቱ ግቦች አካባቢ ውሃ ቋጥረው እንዲሁም ጨቅይተው ተመልክተናል። ይህም ለተጋጣሚዎቹ ቡድኖች ጨዋታውን ምን ያህል ከባድ እንዳደረገባቸው ተመልክተናል።

በጨዋታ ብዛት ከፍተኛ ጫና እየደረሰበት የሚገኘው ስታዲየሙ በቀጣይ ቀናትም እጅግ ወሳኝ ጨዋታዎችን ማስተናገዱ ሲታሰብ በአካባቢው እየጣለ የሚገኘው ዝናብ በዚህ መልኩ የሚቀጥል ከሆነ በተለይ የ10 ሰዓት ጨዋታዎች ለጨዋታ እጅግ ፈታኝ በሆነ ሁኔታ ውስጥ መካሄዳቸው የሚቀር አይመስልም።