ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

ቀጣዩ ትኩረታችን ደግሞ በጨዋታ ሳምንቱ ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች ላይ ያተኮሩ ሀሳቦች የተዳሰሱበት ነው።

👉 ቀጣዩ የሊጉ አብሪ ኮከብ – ብሩክ በየነ

13 ግቦች ላይ የደረሰው ብሩክ በየነ በሰሞነኛ የግብ ማስቆጠር ግስጋሴው ቀጥሎ በመጨረሻው ጨዋታ የሊጉ ከፍተኛ አስቆጣሪ ይሆን ወይ? የሚለው ጉዳይ በጉጉት ይጠበቃል።

በውድድር ዘመኑ ከአንድ ጨዋታ ውጭ በተቀሩት በሙሉ በሀዋሳ ከተማ መለያ ተሰልፎ ሲጫወት የተመለከትነው ብሩክ በየነ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት መከላከያ ላይ ያስቆጠራት ድንቅ የቅጣት ምት ግብ በጣምራ በ14 ግብ የሊጉን ከፍተኛ አስቆጣሪነት እየመሩ ለሚገኙት አቡበከር ናስር ፣ ይገዙ ቦጋለ እና ሪችምንድ ኦዶንጎ በአንድ ግብ አንሶ በ13 ግቦች ከጌታነህ ከበደ ጋር ለመቀመጥ አብቅቶታል።

በመጨረሻ ሰባት የሊግ ጨዋታዎች ሰባት ግቦችን ያስቆጠረው ብሩክ በጀመሩበት መጠን ግቦችን ለማስቆጠር የተቸገሩ አጥቂዎች በበዙበት የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ዝርዝር ከዋነኛ ተዋናዮች ተርታ ለመመደብ በቅቷል። በሊጉ እያሳየ ከሚገኘው ብቃት አንፃር የሚገባውን ያክል ክብር እየተሰጠው የማይገኘው ይህ አጥቂ በቡድን ስራ ውስጥ የሚገኙ ግቦችን ከማስቆጠር ባለፈ ግቦችን ከምንም የሚያስቆጥርበት መንገድ በራሱ እጅግ የተለየ ያደርገዋል።

በሀዋሳ ከተማ መለያ በሊጉ ባለፉት አመታት በወጥ ብቃት ከአመት አመት እያገለገለ የሚገኘው ተጫዋቹ አቡበከር ናስርን ለተነጠቀው ሊጉ ያለጥርጥር የእሱ አልጋ ወራሽ ይሆናል በሚል በብዙዎች ዘንድ ተስፋ ተጥሎበታል። የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ብሩክ በየነ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ እንደሚጨርስ ሙሉ እምነት ይዟል ፤ ከመከላከያው ጨዋታ በኋላም ተከታዩን ብሏል።

“በእርግጠኝነት በቀሪው ጨዋታ ላይ አግብቶ ኮከብነቱን ይወስዳል ብዬ አስባለሁ። አንደኛው አቡበከር ነው ፤ አቡበከር አይጫወትም። የሲዳማው ተጫዋች ይገዙም አለ። ሌሎች ደግሞ የሚጫወቷቸውን ቡድኖች ስታይ የማግባት ዕድላቸው ትንሽ ጠበብ ስለሚል እሱ ይሄን ነገር ያሳካል ፤ ይገባዋል ብዬ ነው የማስበው።”

👉 የጌታነህ ከበደ ተፅዕኖ

ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች በተጣለበት ቅጣት ምክንያት ቡድኑን ማገልገል ሳይችል የቀረው ጌታነህ ከበደ ወደ ጨዋታ በተመለሰበት የ29ኛ ሳምንት መርሃግብር ተፅዕኖው ምን ድረስ እንደሆነ በሚገባ ተመልክተናል።

ወልቂጤ ከተማን በአምበልነት እየመራ ወደ ሜዳ የተመለሰው ጌታነህ ከበደ ገና ከጅምሩ ወደ ሜዳ በመመለሱ ብቻ ምን ያክል የቡድኑ የራስ መተማመን ከሰሞኑ ካደረጓቸው ጨዋታዎች ከፍ ያለ እንደነበር በጨዋታው ለመመልከት ችለናል። ከዚህ ባለፈ ቡድኑ በተለይ በማጥቃቱ ወቅት ፊት ላይ አንድ የንፃሬ ነጥብ (Reference point) እንደማግኘቱ አጠቃላይ የቡድኑ ማጥቃት በተለይ ወደ ማጥቂያው ሲሶ ሲደርስ ኳሶች በሙሉ መዳረሻቸው ጌታነህ የነበረ ሲሆን በዚህም መነሻነት ተጫዋቹ በቡድኑ ማጥቃት ላይ ወሳኙ ሰው ነበር።

ተደጋጋሚ ሙከራዎችን በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ማድረግ የቻለው ጌታነህ በሀይሉ ተሻገር ያስቆጠራት ሁለተኛ ግብ ስትቆጠርም መነሻው እሱ ነበር ፤ ከግቡ ትይዩ ያገኘውን የቆመ ኳስ አጋጣሚ ሀይልን በቀላቀለ ሁኔታ ወደ ግብ የላካት እና በግቡ አግዳሚ ከተመለሰችበት ኳስ ነበር የበሀይሉ ግብ የተገኘችው።

የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን ዝርዝር በጋራ በ14 ግቦች እየመሩ ከሚገኙት ሪችሞንድ አዶንጎ ፣ አቡበከር ናስር እና ይገዙ ቦጋለ በአንድ ግብ አንሶ የሚገኘው ጌታነህ ከበደ በጨዋታው ግብ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልሰመረለትም ፤ ነገርግን ቡድኑን በሊጉ መቆየቱን ያረጋገጠበት ውጤት መመዝገብ ላይ የነበረው ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም።

በሊጉ ለሦስተኛ ጊዜ ከፍተኛ ሆኖ ለማጠናቀቅ እየታተረ የሚገኘው ጌታነህ ከበደ በመጨረሻው የሊግ ጨዋታ ቡድኑ ወላይታ ድቻን ሲገጥም ሁለት እና ከዚያ በላይ ግቦችን ማስቆጠር የሚችል ከሆነ ውጥኑ የሚሰምርለት ይሆናል።

👉በዓመት አንዴ የሚያስገርመን አናጋው ባደግ

ሀዲያ ሆሳዕና እና ወላይታ ድቻ ሁለት አቻ በተለያዩበት ጨዋታ አናጋው ባደግ ያስቆጠራት ግብ ትኩረት የምትስብ ነበረች።

በውድድር ዘመኑ በ28 ጨዋታዎች በድምሩ ለ2465 ያክል ደቂቃዎች ተሰልፎ መጫወት የቻለው አናጋው ባደግ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ወላይታ ድቻዎች በ16ኛው ደቂቃ በተቆጠረባቸው ግብ 1ለ0 እየተመሩ በቀጠለው ጨዋታ አናጋው ባደግ በግራ መስመር ወደ ሀዲያ ሳጥን በቀረበ ስፍራ ያገኘውን ኳስ በግሩም ሁኔታ ከርቀት አክርሮ በመምታት ቡድኑን አቻ ያደረገችን ግብ በአስደናቂ ሁኔታ ማስቆጠር ችሏል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመንም እንዲሁ አንድ ግብ ማስቆጠር የቻለው አናጋው ባደግ ግቧ በተመሳሳይ በባህር ዳር ስታዲየም ቡድኑ በ13ኛ የጨዋታ ሳምንት ሲዳማ ቡናን 1-0 በረታበት ጨዋታ በ48ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ ከመሀል ሜዳ ትንሽ አለፍ ብሎ ያገኘውን አጋጣሚ ተንሸራቶ መሳይ አያኖ መረብ ላይ ያሰራፋት ግብ እጅግ አስደናቂ እንደነበረች አይዘነጋም።

👉 ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን ያደረጉት የወላይታ ድቻ ታዳጊዎች

ወላይታ ድቻዎች ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር 2-2 በተለያዩበት ጨዋታ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በሁለተኛው አጋማሽ በርከት ላሉ ለወጣት ተጫዋቾች የጨዋታ ደቂቃ ሰጥተው ተመልክተናል።

በዚህ ሂደት በጨዋታው ተቀይረው ከገቡ አምስት ተጫዋቾች መካከል አራቱ በሊጉ እስካሁን በቋሚነት ጨዋታ መጀመር ያልቻሉት ተስፈኞቹ መሳይ ኒኮል ፣ ዮናታን ኤልያስ ፣ ሳሙኤል ጃግሶ እና ዘላለም አባቴ ናቸው።

በጨዋታው በተለይ እነዚህ ተጫዋች ወደ ሜዳ ከገቡበት ደቂቃ አንስቶ ተቀዛቅዞ የነበረውን የቡድኑን ማጥቃት ለማሳደግ የነበራቸው ትጋት አስደናቂ የነበረ ሲሆን በተቃራኒው በመከላከሉም እንዲሁ ከፍ ያለ አበርክቶ ለቡድኑ ሰጥተዋል። በጨዋታው በአጥቂ ስፍራ ላይ ቃልኪዳን ዘላለምን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ወጣቱ ዘላለም አባቴ ሁለት እጅግ አደገኛ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ቢያገኝም መረጋጋት ባለመቻሉ ሳይጠቀምባቸው ቀረ እንጂ በአደገኛ ስፍራዎች የተገኘበት ሂደት የሚደነቅ ነበር።

በጨዋታው ከዚህ ቀደም በአንድ ጨዋታ ብቻ ለ52 ያክል ደቂቃዎች ብቻ ተሰልፎ መጫወት ችሎ የነበረው እና በ60ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ዳዊትን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ዮናታን ኤልያስ በ80ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን ያሻማው ኳስ በፍሬዘር ካሳ ተጨርፋ ከመረብ መዋሀዷን ተከትሎ ቡድኑ ሁለት አቻ የሆነበትን አጋጣሚ መፍጠር ችሏል።

በውድድር ዘመኑን እጅግ በጠበበ ስብስብ የገፉት ወላይታ ድቻዎች በእነዚህ ታዳጊ ተጫዋቾች ላይ ይበልጥ እምነት አሳድረው መጠቀም ችለው ቢሆን ኖሮ ከዚህ በሻለ ውጤታቸውን ማሳመር በቻሉ ነበር።

👉 ዑመድን የመሰለው ዑመድ

ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዳግም ከተመለሰ ወዲህ የቀደመ ማንነቱን ፈልጎ ለማግኘት ተቸግሮ የተመለከትነው ዑመድ ዑኩሪ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በተወሰነ መልኩ ከዚህ ቀደም በመከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የምናውቀውን ስል ማንነቱን ተላብሶ ተመልክተናል።

ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ በተጠናቀውው የውድድር ዘመን አጋማሽ ከተመለሰ ወዲህ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በ19ኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ አዳማን ሲረታ ባስቆጠራት ግብ ለወራት የዘለቀውን የጎል ረሃብ ያስታገሰው ተጫዋቹ ያንን ሂደት ማስቀጠል ሳይችል ቀርቶ ሰንብቷል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በሀዲያ ሆሳዕና በኩል እጅግ አስደሳች ጊዜን ያሳለፈው ዑመድ በወላይታ ድቻው ጨዋታ መጀመሪያው አጋማሽ በ16ኛው ደቂቃ ከአበባየሁ ዮሐንስ የደረሰውን ኳስ በተረጋጋ አጨራረስ ያስቆጠረ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ 61ኛው ደቂቃ ደግሞ ፀጋዬ ብርሃኑ ከቀኝ የሳጥን ጠርዝ ያሻማውን ኳስ በግሩም ቅልጥፍና እንዲሁ ማስቆጠር ችሏል።

በዘንድሮው የውድድር ዘመን በአጠቃላይ በ21 ጨዋታዎች ላይ በድምሩ 1395 ደቂቃዎችን በሜዳ ላይ ያሳለፈ ሲሆን በዚህም በአጠቃላይ ያስቆጠረው የግብ ብዛት ሦስት ነው። በራስ መተማመን ረገድ በሚያስገርም መልኩ ወርዶ እያስተዋልነው የሚገኘው የ2006 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የነበረው ዑመድ በዚህ የጨዋታ ሳምንት ያሳየው እንቅስቃሴ ለቀጣይ መነሳሻ ይሆነዋል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 ድንቅ ብቃት ላይ የሚገኘው ኦሴይ ማዉሊ

ባህር ዳር ከተማዎች ፍፁም የበላይ በነበሩት የሰበታ ከተማው ጨዋታ ምንም እንኳን ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት ባይችሉም ኦሲ ማውሊ እንደሰሞኑ ጨዋታዎች ሁሉ ድንቅ ሆኖ ያሳለፈበት ነበር።

በውጤት ረገድ ወጥነት የሚጎድለው ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ጥቂት ጨዋታዎች የቡድኑን ምርጥ ተጫዋች እንምረጥ ብንል ከጋናዊው አጥቂ ኦሴይ ማዉሊ ውጪ ሌላ ተጫዋች ፈልጎ ማግኘት እጅግ ከባድ ነው። በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች አራት ግቦችን በማስቆጠር ከፍፁም ዓለሙ ጋር በጣምራ የባህር ዳር ከተማ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ መሆን የቻለው ማዉሊ በተለይ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አክሮባቲክ በሆነ መንገድ ያስቆጠራት ግብ እጅግ አስብደናቂ ነበረች።

18ኛ ጨዋታውን ለቡድኑ ያደረገው ይህ ጋናዊ አጥቂ በተለይ የቦታ አረዳዱ እጅግ የሚያስደንቅ ነው። የባህር ዳር ከተማን የፊት መስመር እየመራ የሚገባው ማዉሊ በእንቅስቃሴ ወቅት የኳሱን ሂደት አስቀድሞ በመረዳት በተለይም በመስመሮች መካከል ራሱን ነፃ አድርጎ የሚገኝበት እንዲሁም ጀርባውን ለጎል ሰጥቶ ኳሶችን ተቀብሎ የሚዞርበት መንገድ እጅግ አስደናቂ ሲሆን ከዚህ ባለፈ ደግሞ ከሳጥን ውጪ የሚያደርጋቸው ምቶች ለተጋጣሚ ቡድን ግብ ጠባቂዎች እጅግ ፈታኝ ሲሆኑ እያስተዋልን እንገኛለን።

ከሰበታ ጋር አንድ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ተደጋጋሚ አደገኛ ሙከራዎችን ሲያደርግ የነበረው ተጫዋቹ ከአስደናቂዋ ግቡ ባለፈ በአንድ አጋጣሚ ያደረገውን ሙከራ የግቡ ቋሚ ግብ ከመሆን የከለከለው ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በሰለሞን ደምሴ ብቃት ከሽፈውበታል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም በቁጥር በርከት ብለው ጨዋታውን የታደሙት የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች ምንም እንኳን በጨዋታው ውጤት ቅር ቢሰኙም በጨዋታው የቡድናቸውን ብቸኛ ግብ ያስገኘውን እና በግሉ የተቻለው በሙሉ ሲሰጥ ለነበረው ጋናዊው አጥቂ ከፍ ያለ ምስጋና ሲቸሩት ተመልክተናል።

👉 ጦረኛው ወልደአማኑኤል ጌቱ

ምንም እንኳን ሰበታ ከተማ በሊጉ ከፍተኛውን(46) ግቦችን ያስተናገደው ቡድን ቢሆንም ከዚህ ደካማ የመከላከል አወቃቀር ውስጥ ግን ብቸኛ ተስፋ ሰጪ ነገር የወልደአማኑኤል ጌቱ ብቃት ይመስላል።

መከላከል እንደ ቡድን በመዋቅር የሚሰራ ተግባር እንደመሆኑ የሰበታ ከተማ የመከላከል መዋቅር ላይ ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ቢሆንም ወልደአማኑኤል ጌቱ ግን በዚህ ደካማ መዋቅር ውስጥ በግሉ እያሳየ የሚገኘው ጥረት የሚደነቅ ነው። በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና በሚመራው እና በከፍተኛ ሊግ እስከ መጨረሻው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ድረስ በተጓዘው የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስብስብ ውስጥ ያሳየውን ድንቅ ብቃት ተከትሎ ወደ ሰበታ ከተማ ያመራው ወልደአማኑኤል ጌቱ ቀስ በቀስ የቡድኑ ተመራጭ የመሀል ተከላካይ ለመሆን በቅቷል።

የውድድር ዘመኑ ሲጀመር የቀድሞ የቡድኑ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የፕሪሚየር ሊል ልምድ ያላቸውን አንተነህ ተስፋዬ ፣ በረከት ሳሙኤል እና ቢያድግልኝ ኤልያስን ተቀዳሚ ተመራጭ በማድረግ ለመጠቀም መፈለጋቸውን ተከትሎ የመጀመሪያ ጨዋታውን በመጀመሪያ ተሰላፊነት በሰበታ ከተማ መለያ ለማድረግ እስከ 10ኛ የጨዋታ ሳምንት ድረስ ለመጠበቅ ተገዷል።

ከዚህ ጨዋታ በኋላ ግን ቀስ በቀስ በቡድኑ የመሀል ተከላካይ የአማራጭ ዝርዝር ውስጥ ደረጃቸውን እያሳደገ የመጣው ተከላካዩ በ16 ጨዋታውች ላይ በድምሩ 1297 ደቂቃዎችን ተሰልፎ መጫወት ችሏል። በተለይ ከ22ኛ የጨዋታ ሳምንት አንስቶ በቋሚነት በጀመረባቸው ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ እያሳየ የሚገኘው ብቃት እጅግ አስደናቂ ነው። ለመከላከል የተሰጠው ተከላካዩ በተለይ እጅግ ወሳኝ በሆኑ ቅፅበቶች እንቅስቃሴዎችን የሚያቋርጥበት እንዲሁም በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ያለው አፈፃፀም የሚያስደንቁ መገለጫዎቹ ሲሆኑ በተለይ የጨዋታ እንቅስቃሴው ኃይል መቀላቀልን በሚፈልገበት ወቅት የሚያሳየው ቆራጥነት አስገራሚ ነው።

በትልቁ የውድድር እርከን የመጀመሪያ የውድድር ዘመኑን እያሳለፈ የሚገኘው የመሀል ተከላካዩ ባሳለፍነው ዓመት የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ደርሶት የነበረ ቢሆንም በክለቡ በመፈለጉ ቡድኑን ሳይቀላቀል መቅረቱ አይዘነጋም። በመሆኑም አሁን ላይ እያሳየ የሚገኘውን ብቃት ማሳደግ ከቻለ በቀጣይ የብሔራዊ ቡድን ስብስቦች ውስጥ መካተቱ የሚቀር አይመስልም።

👉 ሱራፌል ዳኛቸው እና ጎል ታርቀዋል

የፋሲል ከነማው የአጥቂ አማካይ ሱራፌል ዳኛቸው ከ28 ወራት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በፕሪምየር ሊጉ ጎል አስቆጥሯል።

በፋሲል ከነማ መለያ 21ኛ ጨዋታውን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ያደረገው ሱራፌል ዳኛቸው በዘንድሮው የውድድር ዘመን እስከ ኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ድረስ ስምንት ለግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል ውጤታማ የውድድር ዘመን በማሳለፍ ላይ ቢገኝም ከግብ ፊት ግን ከማቀበል ባለፈ በማስቆጠር ረገድ ዓይናፋር ሆኖ ቆይቷል።

ነገር ግን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ፋሲል ከነማ ኢትዮጵያ ቡናን 3-0 በመርታት በሊጉ ለተወሰኑ ሰዓታትም ቢሆን መሪነቱን በተረከበበት ጨዋታ ላይ ግን የሱራፌል ዳኛቸው ለ28 ወራት የዘለቀ የግብ ረሀብ በመጨረሻው ተገቷል። በጨዋታው በ88ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲል ከነማዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምትን የቡድኑ ተቀዳሚ የፍፁም ቅጣት ምት መቺ የሆነው አምበላቸው ያሬድ ባየህ የመምታት ኃላፊነቱን በጨዋታው ሁለት ግቦች ላስቆጠረው ሙጂብ ቃሲም ቢሰጥም ሙጂብ ከግል ስኬቱ ይልቅ እንደ ቡድን በማሰብ የመምታት ኃላፊነቱን ለሱራፌል ዳኛቸው መስጠቱን ተከትሎ የተፈጠረለትን ዕድል ሱራፌል ዳኛቸው ወደ ግብነት መቀየር ችሏል።

ይህች ግብም በሊጉ በተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመት በ15ኛው ሳምንት የካቲት 15 ላይ ቡድኑ ፋሲል ከነማ በሀዋሳ ከነማ 3-2 በተሸነፈበት ጨዋታ ካስቆጠራት ግብ በኋላ የተገኘች ሲሆን በሁሉም ወድድሮች ደግሞ መስከረም 9 2014 ላይ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የመልስ ጨዋታ አልሂላል ኦምዱርማን ላይ ካስቆጠራት ግብ በኋላ የተገኘች ግብ ሆና ተመዝግባለች።

👉 ሀዋሳ ከተማ ግብ ጠባቂዎች ማምረቱን ቀጥሏል

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ በፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታን ማድረግ የቻለው ወጣቱ ግብ ጠባቂ ምንተስኖት ጊንቦ እንደ መጀመሪያ ጨዋታ ጥሩ የሚባል የጨዋታ ዕለትን አሳልፏል።

ሀዋሳ ከተማ መከላከያን ገጥሞ 2-1 በረታበት ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሰልፎ የተጫወተው ወጣቱ የግብ ዘብ በጨዋታው በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማን በጨዋታ ያቆዩ አደገኛ አጋጣሚዎችን ያመከነ ሲሆን በጥቅሉ በጨዋታው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን ማድረግ ችሏል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ትኩረት የሚስበው ጉዳይ ሀዋሳ ከተማ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ያስተዋወቃቸው አዳዲስ ግብ ጠባቂዎች ጉዳይ ነው። የውድድር ዘመኑ ሲጀመር የሀዋሳ ከተማ ንብረት የነበረው እና በውሰት ውል ወደ ጅማ አባ ጅፋር ካመራ ወዲህ በዘንድሮው የውድድር ዘመን አስደማሚ ብቃቱን ያሳየውን አላዛር ማርቆስን ጨምሮ በዘንድሮው የውድድር ዘመን የጋናዊው መሀመድ ሙንታሪ ተጠባባቂ በመሆን የጀመረው ነገር ግን በሂደት የመጀመሪያ ተሰላፊ በመሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባል እስከመሆን የደረሰው ዳግም ተፈራም የሀዋሳ ከተማ ንብረት ነው።

ከዚህ ባለፈ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የተመለከትነው ወጣቱ ምንተስኖት ጊንቦም በተከታታይ ጨዋታዎች የመሰለፍ ዕድል የሚያገኝ ከሆነ የመሻሻል አቅም ያለው ግብ ጠባቂ መሆኑን ለተመለከተ ክለቡ የውጭ ሀገር ዜግነት ያለው ግብ ጠባቂ የማምጣቱ ጉዳይ ላይ ጥያቄ እንድናነሳ የሚያስገድድ ነው።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንኳን በሶሆሆ ሜንሳ ፣ ቤሊንጋ ኢኖህ እና መሀመድ ሙንታሪ ግቡን እያስጠበቀ የሚገኘው ሀዋሳ የእነዚህ ግብ ጠባቂዎች መምጣት በራሱ ስህተት ባይሆንም ሜዳ ላይ ግን ቡድኑን በሚገባ ጠቅመዋል የሚለው ጉዳይ ስንመለከት በእነዚህ ግብ ጠባቂዎች መምጣት ብቻ የመጫወቻ ደቂቃ በማጣት ዕድገታቸው ላይ ተግዳሮት ገጥሟቸው የነበሩት ግብ ጠባቂዎች ዕድሉን ሲያገኙ እያሳዩ ከሚገኙት አስደናቂ ብቃት አንፃር አካሄዱን ሊያጤን ይገባል ያስብላል።

ያጋሩ