ሪፖርት | ሠራተኞቹ ዓመቱን በድል ቋጭተዋል

ወልቂጤ ከተማዎች ወላይታ ድቻን 2-0 በመርታት የውድድር ዘመኑን በድል ሲቋጩ ጌታነህ ከበደም 14ኛ የውድድር ዘመኑን ግብ በማስቆጠር በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱ ዝርዝር ውስጥ ተካቷል።

ወላይታ ድቻ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ የስድስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል በዚህም ደጉ ደበበ ፣ ያሬድ ዳዊት ፣ አናጋው ባደግ ፣ ንጋቱ ገ/ስላሴ ፣ ሀብታሙ ንጉሴ እና ቃልኪዳን ዘላለምን አስወጥተው በምትካቸው ውብሸት ወልዴ ፣ ዘላለም አባቴ ፣ እንድሪስ ሰዒድ ፣ መሳይ ኒኮል ፣ ዮናታን ኤልያስ ፣ ከነድ ከበደን አስገብተዋል ፤ በአንፃሩ ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ ጅማ አባ ጅፋርን ረቶ ከተመለሰው ስብስብ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም ዳግም ንጉሴ ፣ አብዱልከሪም ወርቁ ፣ ሀብታሙ ሸዋለም እና አቡበከር ሳኒን አስወጥተው በምትካቸው ፍፁም ግርማ ፣ ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ ፣ አክሊሉ ዋለልኝ እና መሐመድ ናስርን በመጀመሪያ ተሰላፊነት አስጀምረዋል።

ቀዝቀዝ ያለአጀማመር በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ ወልቂጤ ከተማዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻን ወስደው ለመጫወት ጥረት ያደረጉ ቢሆንም የግብ እድሎችን በመፍጠር ረገድ በጥንቃቄ ለመጫወት ሲጥሩ እንደነበሩት ወላይታ ድቻዎች ሁሉ ረገድ እጅግ ደካማ ነበሩ።

በጨዋታ የመጀመሪያው ጠንካራ ሙከራ በ19ኛው ደቂቃ የተመዘገበ ነበር ፤ 19ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ወደ ግራ ካደላ አቋቋም በቀጥታ ወደ ግብ ልኮ ለጥቂት ወደ ውጭ በወጣችበት አጋጣሚ ሲሆን በደቂቃዎች ልዮነት በተመሳሳይ ጌታነህ ከበደ በረጅሙ ከጣለ ኳስ በተነሳ ኳስ የተፈጠረለትን እድል በግንባሩ ገጭቶ ጥሩ ሙከራ አድርጓል።

በአጋማሹ እምብዛም ጨዋታውን መቆጣጠር የተቸገሩት ወላይታ ድቻዎች ጨዋታው ወደ ውሀ ሰዓት እረፍት ከማምራቱ በፊት በፈጣን የማጥቃት ሂደት በቀኝ መስመር በኩል አበባየሁ አጪሶ ከከነን ከበደ ጋር በፈጣን ቅብብል ያለፉትን ኳስ አበባየሁ አጪሶ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ ወጥቶበታል።

ከዚህች ሙከራ በኃላ በተወሰነ መልኩ መነቃቃትን ያሳዩት ወላይታ ድቻዎች በ31ኛው ደቂቃ ከነድ ከበደ በቀኝ የሳጥን ጠርዝ ወደ ፊት ይዞ የገሰገሰውን ኳስ በተሻለ አቋቋም ላይ ለነበረው አበባየሁ አጪሶ አቀብሎት ያደረገው ሙከራ በሮበርት ኦዶንካራ ድኖበታል።

በመጠኑም ቢሆን በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃ ተነቃቅቶ በቀጠለው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በተሻለ መልኩ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ ጥረት ቢያደርጉም አደገኛ የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር ሳይችሉ አጋማሹ ተጠናቋል።

እንደመጀመሪያዎቹ ሁሉ በጠሩ የግብ ሙከራዎች ረገድ ተቀዛቅዞ በቀጠለው ጨዋታ ምናልባት በ54ኛው ደቂቃ ዮናታን ኤልያስ ከሳጥን ውጭ በግራ እግሩ አክርሮ ከሞከረው ኳስ ውጭ መሀል ሜዳ ላይ ከሚቆራረጡ ኳሶች ባለፈ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ለመመልከት ተቸግረናል።

60ኛው ደቂቃ ላይ ወልቂጤ ከተማዎች ቀዳሚ መሆን ችለዋል ፤ አክሊሉ ዋለልኝ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ወደ ሳጥኑ ዘግይቶ የደረሰው እና ከደቂቃዎች አስቀድሞ ተቀይሮ የገባው ቤዛ መድህን በግራ እግሩ መሬት ለመሬት በመምታት አስቆጥሯል።

አቻ ለመሆን የተሻለ ጫና መፍጠር የጀመሩት ወላይታ ድቻዎች በጨዋታው የተሻለ አደገኛ በነበረው የቀኝ መስመር በኩል ተደጋጋሚ እድሎችን ለመፍጠር ሙከራ አድርገዋል ፤ በ69ኛው ደቂቃ ዘላለም አባቴ ከርቀት ያደረገው ሙከራ እንዲሁም በ76ኛው ደቂቃ ዮናታን ኤልያስ በግራ ሳጥን ጠርዝ ያደረገው ሙከራ ሌላው ተጠቃሽ አጋጣሚ ነበር።

በ79ኛው ደቂቃ በረጅሙ በተጣለ ኳስ ከሮበርት ኦዶንካራ ጋር አንድ ለአንድ የተገናኘው ቢኒያም ፍቅሬ ያገኘውን አጋጣሚ ሮበርት አድኖበታል።

በጨዋታው ምንም እንኳን ድቻዎች አቻ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ወልቂጤ ከተማዎች ግን መከላከል ላይ የተጠመዱ በመሰሉበት ሂደት ተጨማሪ ግብ ሳይጠበቁ አግኝተዋል ፤ የጨዋታው መደበኛ ደቂቃዎች መጠናቀቂያ ላይ ወልቂጤ ከተማዎች በረጅሙ የላኩትን ኳስ ለመከላከል በረከት ወ/ዮሀንስ እና ቢኒያም ገነቱ ሳይግባቡ የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅሞ ጌታነህ ከበደ የውድድር ዘመኑን 14ኛ ግብ አስቆጥሮ የቡድኑን አሸናፊነት አረጋግጧል።

ጨዋታው በወልቂጤዎች የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ ነጥባቸውን ወደ 38 በማሳደግ ወደ 8ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች በ42 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ቀጥለዋል።

ያጋሩ