ለከርሞ በፕሪሚየር ሊጉ እንደማይሳተፍ የተረጋገጠው ሰበታ ከተማ የዕግድ ውሳኔ ተላልፎበታል።
ከሜዳ ውጭ ባሉ ችግሮች እየታመሰ የውድድር ዘመኑን ወራጅ በመሆን ያጠናቀቀው ሰበታ ከተማ የወራት ደሞዝ አልተከፈለንም በማለት ቢያድግልኝ ኤልያስ እና አለማየሁ ሙለታ ከዚህ ቀደም አቤቱታቸውን ለዲሲፒሊን ኮሚቴ አሰምተውበት እንደነበር ይታወቃል። አቤቱታውን የመረመረው የዲሲፒሊን ኮሚቴ ሰበታ ከተማ የደሞዝ ክፍያውን እንዲከፍል ውሳኔ ቢያሳልፍም በተቀመጠው ቀነ ገደብ ሰበታዎች ተግባራዊ አለማድረጋቸውን ተከትሎ በድጋሚ ሁለቱ ተጫዋቾች ለፌዴሬሽኑ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
የተጫዋቾቹ የሕግ አማካሪ እና ወኪል የሆኑት አቶ ብርሀኑ በጋሻው እንዳደረሱን መረጃ ከሆነ ሰበታ ከተማዎች ክፍያውን በተቀመጠው ቀነ ገደብ ባለመፈፀማቸው ምክንያት ከቀጣዩ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ጀምሮ የታገዱ መሆናቸውን ፌዴሬሽኑ በደብዳቤ አሳውቋል።