ሪፖርት | ሰበታ ከተማ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ በማሸነፍ ሊጉን ተሰናብቷል

መውረዳቸውን ያረጋገጡት ሰበታ ከተማዎች በፍፁም ገብረማሪያም የፍፁም ቅጣት ምት ጎል አርባምንጭን በማሸነፍ የውድድር ዓመቱ ጉዟቸውን ጨርሰዋል።

ሰበታ ከተማ ከባህር ዳሩ ጨዋታ መልስ ዮናስ አቡሌ ፣ አንተነህ ናደው ፣ ሀምዛ አብዱልመን እና አንተነህ ተስፋዬን በጌቱ ኃይለማሪያም ፣ በረከት ሳሙኤል ፣ ጋብርኤል አህመድ እና ሳሙኤል ሳሊሶ ቦታ አስገብቷል። በአርባምንጭ ከተማ በኩል በቅዱስ ጊዮርጊሱ ሽንፈት የተሰለፉት ወርቅይታደስ አበበ ፣ መላኩ ኤልያስ ፣ እንዷለም አስናቀ እና ፀጋዬ አበራ በጉዳት ፣ ቅጣት እና ታክቲካዊ ምክንያቶች በተካልኝ ደጀኔ ፣ መሪሁን መስቀሌ ፣ ሙና በቀለ እና አሸናፊ ኤልያስ ተተክተዋል።

ቀዝቃዛ የጨዋታ እንቅስቃሴ የተስተዋለት ጨዋታ ቀዳሚ አጋማሽ በአመዛኙ በአርባምንጭ ከተማ የኳስ ቁጥጥር የተከናወነ ነበር። ቡድኑ 8ኛው ደቂቃ ላይ በፈጠረው ዕድል ሱራፌል ዳንኤል ከእንዳልካቸው መስፍን ከተነሳ እና አንተነህ ናደው ለምግኘት ሞክሮ ካልተሳካለት ኳስ ግልፅ የግብ ዕድል አግኝቶ አምክኗል። አዞዎቹ በብልጫቸው ሲቀጥሉ በቁጥር በርክተው ሳጥን ውስጥ የተገኙባቸውን ቅፅበቶች ጨምሮ አህመድ ሀሴን ፣ አሸናፊ ኤልያስ ፣ እና መሪሁን መስቀሉ ግማሽ ሊባሉ የሚቹሉ ዕድሎች አግኝተው ወደ አደገኛ ሙከራነት መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ከውሃ ዕረፍቱ በኋላ ሰበታ ከተማዎች በመጠኑ ተነቃቅተው ሲታዩ አጥቂያቸው ፍፁም ገብረማሪያምን ያማከሉ ፈጣን ሽግግሮችን ያደረጉባቸው ቅፅበቶች ታይተዋል። ከእነዚህ ውስጥ የተሻለ በነበረው አጋጣሚ አብዱልሀፊስ ቶፊቅ ባስጀመረው መልሶ ማጥቃት ዱሬሳ ሹቢሳ 32ኛው ደቂቃ ላይ ለፍፁም ባደረሰው ኳስ አጥቂው ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም ሙከራው ይስሀቅ ተገኝን የሚፈትን አልሆነም።

ሁለተኛው አጋማሽን ቡድኖቹ ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ቢጀምሩም በጥሩ የማጥቃት ምልልስ ፍንጭ የሰጠው አጀማመር 66ኛው ደቂቃ ወደ ግራ ካደላ የርቀት ቅጣት ምት አሸናፊ ኤልያስ አስደናቂ ሙከራ አድርጎ በግቡ አግዳሚ እስከመለሰበት ጊዜ ድረስ የግብ አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ አልተመለከትንም። በጨዋታው በበጎው የሚነሳው ወጣቶቹ የሰበታው ቶማስ ትዕግስቱ እና የአርባምንጩ አላዛር መምሩ የጨዋታ ጊዜ የማግኘታቸው ጉዳይ ነበር።

ሆኖም ግን ዕድለኛ ያልነበረው የአርባምንጩ አላዛር በሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተነሳ ሰበታ ከተማ የፍፁም ቅጣት ምት ያገኘ ሲሆን 75ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ገብረማሪያም ወደ ግብነት ቀይሮታል። 

ከብቸኛዋ ግብ በኋላ አርባምንጮች የመጀመሪያ አጋማሽ ጫናቸውን መልሰው ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም የአቻናቷን ግብ ሳያገኙ ጨዋታው በሰበታ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ አርባምንጭ ከተማ በ40 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ሲቆይ ሰበታ ከተማ ነጥቡን 25 አድርሶ ወደ 15ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።