የትንቅንቁ ተፋላሚዎች መንገድ – ክፍል 2

የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማን የነገ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች መነሻ በማድረግ የቡድኖቹን ጉዞ የቃኘንበት ሁለተኛ እና የመጨረሻ ክፍል እንዲህ ይነበባል…

ከሰዓታት በፊት ለንባብ ባበቃነው የመጀመሪያው ክፍል ፅሁፍ የዋንጫ ተፋላሚዎቹ ከውድድሩ መጀመር በፊት የነበራቸውን ጊዜ እና በውድድሩ አስተናጋጅ ከተሞች ቆይታ ስላለፉበት የውድድር ጊዜ አንስተናል። አሁን ደግሞ በዚሁ ሂደት ውስጥ ሊነሱ ከሚገባቸው እና ለተመዘገቡት ውጤቶች ወሳኝ ከነበሩ ነጥቦች ላይ ተኩረት አድርገናል።

የሹም ሽር ውሳኔዎች…

በሁለቱ ተፎካካሪ ክለቦች የዘንድሮ ጉዞ ውስጥ የውድድር ምዕራፎችን ከቀየሩ ውሳኔዎች ውስጥ በተመሳሳይነት ከሚነሱ ነገሮች ዋነኛው የአሰልጣኝ ለውጥ ነው። አሁን ላይ ሁለቱም ዓመቱን አብረው የጀመሩ ዋና አሰልጣኞቻቸው ጋር ተለያይተው ለምክትሎቻቸው በሰጡት ኃላፊነት ዓመቱን ለመጨረስ ተቃርበዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ አምና በሆላንዳዊው አርነስት ሚድንድሮፕ ፣ በደቡብ አፍሪካዊው ማሂር ዴቪድስ እና በእንግሊዛዊው ፍራንክ ናታል ቅብብሎሽ የጨረሰው የውድድር ዓመት በሹም ሽር የተሞላ ነበር። ክለቡ ዘንድሮም በጀመረበት ለመጨረስ አልታደለም። በክረምቱ ነሐሴ 10 ላይ ቅጥራቸው ይፋ የሆነው ሰርቢያዊው ዝላትኮ ክራምፖቲች
በቅድመ ውድድር ጊዜ ከቡድኑ ርቀው የሰነበቱበት አጋጣሚ የበዛ ሲሆን ውድድሩ ሲጀምርም በአንደኛ ሳምንት ከሰበታ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ከታዩ በኋላ ዳግም ጠፍተዋል። በመቀጠል ሦስተኛውን የመከላከያ እና ቀጣዩን የሲዳማ ቡና ጨዋታ ከመሩ በኋላ ኋላ ላይ በክለቡ አመራሮች እንደተባለው ከተጫዋቾች ጋር ግጭት ውስጥ ይገቡ የነበሩት አሰልጣኝ በጊዜ ከክለቡ ጋር መለያየታቸው እውነት ሆኗል። በዚህ ረገድ ከአምናው ዘንድሮ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት የተለየው ጉዳይ ኃላፊነቱን ለሌላ የውጪ ዜጋ ከመስጠት ይልቅ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታን ከደረጄ ተስፋዬ እና ቀሪ የሀገር ውስጥ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ጋር እንዲቀጥል ማድረጉ ነበር። በዚህም ውሳኔ ቡድኑ በአምስት ጨዋታዎች አንድ ድል ብቻ ካስመዘገበበት አጀማመር ወጥቶ ከላይ ባቀረብነው ጉዞ ውስጥ በማለፍ በሊጉ አናት ወደ መጨረሻው የሊጉ ሳምንት እንዲሸጋገር ሆኗል።

በሌላኛው ካምፕ ከውድድሩ ጅማሮ በፊት በውስጣቸው ስጋት የነበረው የወቅቱ የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ስለቻምፒዮኑ ቡድናቸው ቀጣይ ዓመቱ ጉዞ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ይህንን ብለው ነበር። …“አንድ ቡድን ቻምፒዮን መሆኑ የሚታወቀው በስተመጨረሻ ነው። በመሐል ላይ ውጣ ውረዶች ሊኖሩ ስለሚችሉ ደጋፊዎቻችን ሁሌም በትዕግስት መጠበቅ አለባቸው።…” ታዲያ ውድድሩ ሲጀምር የአሰልጣኙ ስጋት በጥሩ አጀማመር የተቀረፈ ቢመስልም ከአፄዎቹ ጋር የነበራቸው ጉዞ ግን ከ17 ሳምንታት በላይ መዝለቅ አልቻለም። የውጤት መጥፋት በትር ዞሮ ዞሮ አሰልጣኞች ላይ የማረፉ ነገር የሚቀር ባይሆንም ፋሲል ከነማ ቀድሞ ከነቃው ቅዱስ ጊዮርጊስ አንፃር በዚህ ረገድ የታየበት መዘናጋት ምንአልባትም አሁን ላይ እጅግ የሚቆጭበት ይመስላል። ይህንን ለመረዳት ቁጥሮችን በስሱ መመልከት በቂ ነው። ቡድኑ ከአሰልጣኝ ስዩም ጋር በ17 ጨዋታዎች 27 ነጥቦችን ሲያሳካ ወደ ዋና አሰልጣኝነት ካመጣቸው አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ ጋር ደግሞ በ12 ጨዋታዎች 34 ነጥቦችን አሳክቷል።

የውድድር ዓመቱ ወሳኝ እጥፋቶች

እስከ 30ኛው ሳምንት የቀጠለው የዘንድሮው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የቻምፒዮንነት ፍትጊያ የኃይል ሚዛኑን ከአንዱ ወደ ሌላኛው ክለብ የቀየሩ ጨዋታዎች ነበሩ። በፋሲል ከነማ በኩል 4ኛው ሳምንት ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ያስተናገደውን ሽንፈት በዚህ ረገድ የሚነሳ ነው። በዓመቱ ያልጠበቁ ውጤቶች ከተመዘገቡበት ጨዋታ አንዱ በሆነው በዚህ ጨዋታ ሦስት ተከታታይ ድሎችን አሳክቶ ሊጉን የጀመረው ፋሲል በአዲስ አዳጊ ቡድን በመጀመሪያ አጋማሽ 2-0 መመራቱ እና በመጨረሻም 2-1 መረታቱ አግራሞትን የጫረ ነበር። በመሆኑም ዐፄዎቹ ሊጉን እንደአጀማመራቸው አምና እንዳደረጉት በሰፊ የነጥብ ልዩነት ሊጨርሱ ይችላሉ የሚለው ዕምነት እንዲፋለስ ምክንያት የሆነ ጨዋታ ነበር ማለት ይቻላል።

በመቀጠል 10ኛ ሳምንት ላይ ስንመጣ በድሬዳዋው ውድድር ቀዳሚ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ፋሲል ከነማን 4-0 የረታበትን ጨዋታ እናገኛለን። ይህ ጨዋታ ፈረሰኞቹ የቅርብ ተፎካካሪያቸውን በአደናቂ ብቃት ድል ማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን የሊጉን መሪነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተረከቡበት መሆኑም የውድድሩ ሌላ ምዕራፍ ጅማሮ ተደርጎ እንዲወሰድ የሚያደርግ ነበር። በመቀጠል 13ኛ እና 14ኛ ሳምንት ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሀዲያ ሆሳዕና እና አርባምንጭ ከተማ በተከታታይ ነጥብ የጣለባቸው ጨዋታዎች ይጠቀሳሉ። ከእነዚህ ጨዋታዎች በፊት አምስት ተከታታይ ድሎችን ያሳካው የ14 ጊዜ ቻምፒዮኑ የማይበርድ የመሰለው ጉዞ ቀዝቀዝ ያለባቸው ሁለቱ ጨዋታዎች የዋንጫ ፉክክሩ በሁለተኛው ዙር በተጠባቂነቱ እንዲቀጥል አስተዋፅዖ ነበራቸው።

በመቀጠል 18ኛው ሳምንት ላይ ስንመጣ ፋሲል ከነማ በጅማ አባ ጅፋር ላይ ያስካውን ድል እናገኛለን። ይህ ጨዋታ የቡድኑ መስፈንጠሪያ ተደርጎ ይወሰዳል። ከአሰልጣኝ ሹም ሽሩ በኋላ ያልቆመ የድል ጉዞው በጅማው ድል የጀመረ ሲሆን በመቀጠል የገጠመው አዲስ አበባ ከተማ ነጥብ ቢያስጥለውም ከዛ በኋላ ግን እስካሁን ድረስ ፋሲል በድል ጎዳና ላይ መጓዙን ቀጥሏል።

ቀጣዩ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው የ25ኛ ሳምንቱ የሁለቱ ቡድኖች እርስ በእርስ መገናኘት ነበር። እጅግ ከባድ ውጥረት የነበረበትን ያንን ጨዋታ ፋሲል ከነማ 1-0 ማሸነፍ መቻሉን ተከትሎ ከ10 ጀምሮ ሲሸረሸር የከረመው የቡድኖቹ ልዩነት በግማሽ ቀንሶ አምስት የደረሰበት ሆኗል። የስድስት ነጥቦች ዋጋ ያለውን ጨዋታ ሊያውም ቀጥተኛ ተፎካካሪውን ማሸነፍ ለፋሲል ከነማ ተስፋ መፈንጠቅ ትልቅ ዋጋ ነበረው።

ከዚህ በመቀጠል 29ኛው ሳምንት ላይ ስንመጣ ደግሞ ፈረሰኞቹ አዞዎቹን በ1-0 ውጤት የረቱበትን ወሳኝ ፍልሚያ እናገኛለን። ከጨዋታው በፊት በጊዮርጊስ እና ፋሲል እስካሁን የዘለቀ ፍትጊያ ከረጅም ሳምንታት በኋላ ቀድሞ የተጫወተው ፋሲል ከነማ ሀዋሳ ከተማን መርታቱን ተከትሎ ከ9ኛው ሳምንት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መሪ መሆን ችሎ ነበር። በመሆኑም ከማሸነፍ ውጪ ሌላ ምርጫ ያልነበራቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች አርባምንጭን መርታት መቻላቸው ምንአልባትም የዓመቱ እጅግ ወሳኝ ድል ሆኖ የሚመዘግብላቸው ነበር። ይህንን ማድረግ መቻላቸውም ለሰዓታት አጥተውት የነበረውን መሪነት ዳግም በማስመለስ ወደ 30ኛው ሳምንት እንዲሻገሩ አድርጓቸዋል።

ወሳኝ የነበረው የደጋፊዎች አስተዋፅዖ

በዓለም ዙሪያ ብዙ ነገር ያዛባው የኮቪድ 19 ወረርሺኝ በ1990 በአዲስ ፎርማት የጀመረውን የኢትዮጵያን ከፍተኛውን የሊግ እርከንም አንድ የውድድር ዓመት ነጥቋል። ከዛ ባለፈ ዓምናም በውስን ደጋፊዎች ብቻ ታጅቦ መከናወኑ የእግርኳስ የልብ ምት የሆነውን ድባብ ማስቀረቱ የውድድሩን ማራኪነት ቆሌ የራቀው አድርጎት ነበር። ወረርሺኙ ጋብ ባለበት የያዝነው ዓመት ግን የለመድነው የደጋፊዎች አጀብ በአስተናጋጅ ስታድየሞች ውስጥ መታየት መጀመሩ የውድድሩን ውበት መልሶታል። ከዚህ ባለፈም የደጋፊዎች አስተዋፅዖ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ከፍ ያለ ድርሻ እንደነበረው መናገር ይቻላል።

ይህንን ነጥብ በድጋሚ ዓመቱን በአዘጋጅ ከተሞች ከፋፍለን እንድንመለከት ያደርገናል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ቅዱስ ጊዮርጊስም ሆነ ፋሲል ከነማ የተሻለ ግስጋሴ እንዲያደርጉ የደጋፊዎቻቸው እገዛ አስፈላጊ ስለመሆኑ እንረዳለን። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአራቱ ከተሞች የተሻለ የ88% የነጥብ መሰብሰብ ጉዞ ባደረገባት አዳማ ከተማ ላይ በነበረው የውድድር ጊዜ ከመቀመጫ ከተማው አዲስ አበባ ቅርበት አንፃር በበርካታ ደጋፊዎቹ ታጅቦ ያደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ ስኬቱ ከፍ ማለቱ ከውጤቱ ጀርባ ስለነበሩ ደጋፊዎቹ የሚነግረን ነገር አለ። በተመሳሳይ
ፋሲል ከነማ ለጎንደር ቀርቦ ባህር ዳር ላይ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ሙሉ በሙሉ የማሸነፍ ግስጋሴውን ሲያደርግ የደጋፊዎቹ በብዙ ቁጥር መገኘት ወሳኝ ነበር። ከሁሉም በላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን በረታበት እና በፉክክሩ እንዲዘልቅ ትልቅ አስተዋፅዖ የነበረውን ጨዋታ በበርካታ ደጋፊዎቹ ፊት ማድረጉ በእጅጉ ጉልበት ሆኖታል።

ነገ የሊጉ ወሳኝ የመጨረሻ ጨዋታዎች ሲደረጉም እንዲሁ ድልን ለማጣጣም ከማሰብ ባለፈ በቡድናቸው ውጤት ላይ ቀጥተኛ አስተዋፅዖ ለማድረግ ከአዲስ አበባ እና ከጎንደር በርካታ ደጋፊዎች ወደ ባህር ዳር እንደሚተሙ ይጠበቃል።

የግል እና የዲፓርትመንት አስተዋፅዖዎች

መቼም የቡድን ስኬት እና ድክመት ውስጥ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የግለሰቦች አስተዋፅዖ በየፈርጁ መኖሩ የግድ ነው። እግርኳስ የቡድን ሥራ እንደመሆኑም የዲፓርትመንትም የአጠቃላይ ቡድንም መጣጣም እና ወጥነት አብዝቶ ያስፈልጋል። ከእነዚህ ነጥቦች አንፃር የዘንድሮው የዋንጫ ተፋላሚዎችን ጉዞ ስንቃኝም ትኩረት የሚስቡ ጉዳዮች መኖራቸው አልቀረም። ምንም እንኳን ርዕሱ ሰፊ ቢሆንም በዋናነት ከጨዋታ ደቂቃዎች ፣ ከግብ አስቆጣሪዎች እና ግብ የሆኑ ኳሶችን ካመቻቹ ተጨዋቾች በመነሳት የተወሰኑ ነገሮችን ለመመልከት እንሞክራለን።

ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ ዝቅተኛ ግብ ያስተናገደ (11) ቡድን ነው። ወደ ቀደመ የጨዋታ ዘይቤው ባዘነበለበት የዘንድሮው የውድድር ዓመት በጠንካራ የመከላከል መሰረት ላይ ተገንብቷል። የኋላ መዋቅሩ ከጥንካሬው በለፈም በተጫዋቾች ምርጫ ወጥ ነበር። ለዚህም ነው ዘንድሮ ቡድኑን ለረጅም ደቂቃዎች ያገለግሉ ተጫዋቾችን ስናስቀምጥ የመጀመሪያ አራቱ ምኞት ደበበ ፣ ኤድዊን ፍሪምፖንግ ፣ ቻርለስ ሉኩዋጎ እና ሄኖክ አዱኛ ሆነው የምናገኛቸው። ለረጅም ደቂቃዎችን ከማገልገል እና ጥብቅ መከላከልን ከመዘርጋት ባለፈ ቀጥተኛ እና ተሻጋሪ ኳሶችን በሚያዘወትረው የዘንድሮው የፈረሰኞቹ አጨዋወት ውስጥ የኋላ ክፍሉ ተሰላፊዎች በድምሩ ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥሩ አምስት ግብ የሆኑ ኳሶችን ማመቻቸት ችለዋል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ የዘንድሮው ስኬት ቁልፍ ጥንካሬ የሆነው ግቦችን ከተለያዩ ምንጮች የማግኘትን ጉዳይ አማካይ ክፍሉ ላይም እናገኘዋለን። የቡድኑ ዋነኛ ፈጣሪ አማካይ የሆነው ከነዓን ማርክነህ ሁለተኛው የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ መሆኑን ማየት ለዚህ በቂ ነው። ለምሳሌ ያህል ከመጨረሻ አስር ጨዋታዎች ስድስቱን ብንወስድ ቡድኑ 16 ነጥቦችን እንዲያሳካ ምክንያት የሆኑ ስምንት ግቦችን ከአማካይ ክፍል ተጫዋቾቹ ማግኘቱን እንረዳለን። ከአጥቂ ክፍሉ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ብዙ ጨዋታዎች ቢያመልጡትም 10 ግቦች ማስቆጠሩ ፣ ጉዳት አላላውስ ያለው አቤል ያለው እና በተለያዩ ሚናዎች ቡድኑን ያገለገለው አማኑኤል ገብረሚካኤል በጋራ 9 ግቦች ማበርከታቸው በሌላው የቡድኑ ክፍሎች ባይታገዝ ለጊዮርጊስ ምን ያህል ፈታኝ ሊሆን ይችል እንደነበር መገመት አያዳግትም። ከዚህ ውጪ አማኑኤል እና ሀይደር አራት አራት ግብ ይሆኑ ኳሶችን በማቀበል ከፍ ያለ አበርክቶ እንደነበራቸው ማንሳት ይቻላል።

በጥቅሉ ሲታይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጠንካራውን የመከላከል ክፍሉን በአግባቡ የሚያግዝ እና ከፍ ያለ የግብ ድርሻ ያለው የአማካይ ክፍል እንደነበረው ከላይ የተነሱት ቁጥሮች ያመለክታሉ። የቡድኑ የስብስብ ጥልቀት በታታሪነት ወደ ኋላ ተመልሶ ክፍተቶችን ለመድፈንም ሆነ ቡድኑ በሚፈልገው ፈጣን ሽግግር ውስጥ በቶሎ ከፊት በመገኘት ተሻጋሪ ኳሶችን በማድረስም ሆነ አደጋ ክልል ላይ ደርሶ ዕድሎችን በመጠቀሙ ረገድ የተዋጣለት ሊባል የሚችል ጊዜን አሳልፏል። እርግጥ ነው በጥልቀት የሚከላከሉ ቡድኖች ሲገጥሙት የተቸገረባቸው ጊዜያት የነበሩ ቢሆንም በተለይም በብዛት እና በጥራት ወደ ሳጥን የሚደርሱ ተሻጋሪ ኳሶቹ ለቡድኑ መላ ሆነው በተደጋጋሚ ውጤት ይዞ እንዲወጣ አስችለውታል። በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ በአፈፃፀም መንገዱ ዋነኛ መሳሪያው የሆነው በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ከፍ ባለ ጉልበት ጨዋታዎችን በመጀመር ግቦችን ማስቆጠር እና ተጋጣሚ በቀሪ ደቂቃዎች ይበልጥ ክፍተት እንዲፈጥር ማድረግ መገለጫው ሆኖ ተመልክተነዋል።

ፋሲል ከነማ

ፋሲል ራሱን ሆኖ በተገኘባቸው ጨዋታዎች ተጋጣሚዎቹን ጫና ውስጥ የሚከትባቸው መንገዶች እምብዛም አልተቀየሩም። ከሜዳው ኳስ መስርቶ የሚወጣ በሚዋልል የአማካይ ክፍል ምርጫ በአስፈላጊ ቦታዎች ላይ የቁጥር ብልጫ የሚፈጥር እና አስፈላጊ ሲሆን በቶሎ ወደ ግብ የመድረስ መንገድንም የሚጠቀም ባለብዙ የማጥቃት መላ ባለቤት ነው። በዋናነት የማጥቃት መንገዶቹ መዳረሻ የሆኑት ሁለቱን ኮሪደሮች የሚመሩት በረከት ደስታ እና ሽመክት ጉግሳ ከግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኬ ጋር በርካታ ደቂቃዎችን ያገለገሉ ተጫዋቾች ናቸው። ስለማጥቃት መንገዱ አማራጮች ስናወራ እና ፋሲል ከነማ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ (47) መሆኑን ስናስብ አምና ከሙጂብ እንዳገኛቸው 20 ጎሎች በወጥነት የሚያገለግል ግብ አስቆጣሪ ያለመያዙን ነገር እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁሉ የግብ ማስቆጠሪያ አማራጮቹ ብዙ እንደነበሩ መረዳት እንችላለን።

ፊት መስመር ላይ ኦኪኪ አፎላቢ እና ፍቃዱ ዓለሙን ብቻ በዋና አማራጭነት ይዞ የጀመረው ፋሲል በወሳኝ ሰዓት ላይ ሙጂብ ቃሲምን ከምርጥ ብቃቱ ጋር አግኝቶ ከሦስትዮሹ ጥምረት 20 ግቦችን አግኝቷል። በተለይ ሙጂብ እጅግ ባስፈለገበት ሰዓት ፋሲል ከሀዋሳ ከተማ እና አዳማ ከተማ ስድስት ነጥቦችን ሲወስድ ሁሉንም ግቦች ሲያስቆጥር በኢትዮጵያ ቡናው ድል ደግሞ ሁለት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ወደ አማካይ ክፍሉ ስንመጣ ለአጥቂው የቀረበ ስድስት ተጫዋቾች የተሳተፉበት የ19 ግቦች አበርክቶ እናገኛለን። እዚህ ላይ ከላይ ካነሳናቸው ሽመክት እና በረከት ሌላ ከመሀል ሜዳ ዘግይቶ በማድረስ ስድስት ግቦችን ያስመዘገበው በዛብህ መለዮ የዘንድሮው አስተዋፅዖ አስደናቂ ነበር።

ስለግብ አስቆጣሪዎች ሲወራ ከአንድ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ውጪ ያልተሳካለት ሱራፌል ዳኛቸው ደጋግሞ የግቡን ብረቶች ሲያጎን የቆየበት የውድድር ጊዜን አሳልፏል። ሆኖም ግን በተለይ ቡድኑ የተጋጣሚን የመከላከል መዋቅር ለማስከፈት ሲቸገር ከተጫዋቹ እግር የሚነሱ እና መካከለኛ ርቀት ያላቸው ያለቁ ኳሶቹ ለፋሲል እጅግ ወሳኝ ነበሩ። በዚህም ስምንት ግብ የሆኑ ኳሶቹ ትልቅ አስተዋፅዖ ነበራቸው። ለግብ በማመቻቸት በሰባት ኳሶች ተከታይ የሆነው በረከት ደስታ ግን አምስት ግቦችን ማስቆጠሩ ሲታሰብ እና በርካታ ደቂቃዎችንም በማገልገል ቀዳሚ መሆኑ ሲጨመርበት የዘንድሮው የፋሲል ኮከብ ነበር ማለት ይቻላል። ፋሲል ከነማ በዚህ ጥሩ የማጥቃት ተዋፅዖው ውስጥ እንደ አምናው ሁሉ ከ4-1-4-1 አሰላለፍ ጋር ተስማምቶ የተመለከትነው ሲሆን በሦስት የኋላ መስመር ተሰላፊዎች የጀመረባቸው አጋጣሚዎች ግን ዋጋ አስከፍለውታል ማለት ይቻላል። በጥቅሉ የኋላ መስመሩ ከጀርባ ለሚጣሉ ኳሶች ተጋላጭ ሆኖ መታየቱ እና ግብ በማስቆጠር እና በማመቻቸት ረገድም የነበረው ድርሻ መቀነሱ ድክመቱ ሆኖ የሚነሳ ነው።

ማጠቃለያ…

በሁለቱ ፅሁፎቻችን የነካካናቸው ነጥቦች እና በሰፊው የሚተነተኑ ሌሎች በርካታ መለኪያዎች ተደማምረው ሁለቱን ተፋላሚዎች ለመጨረሻ የጨዋታ ቀን አድርሰዋቸዋል። ይህም ፕሪምየር ሊጉ በአዲስ ፎርማት ከጀመረበት ጊዜ በኋላ ሰባተኛው አጋጣሚ ይሆናል።

1990 ላይ መብራት ኃይል እና ኢትዮጵያ መድን ፣ 1995 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አርባምንጭ ከተማ ፣ 1996 ላይ ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ፣ 2003 ላይ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት ፣ 2010 ላይ ጅማ አባ ጅፋር እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ 2011 ላይ መቐለ 70 እንደርታ ፣ ፋሲል ከነማ እና ሲዳማ ቡና በዚህ የመጨረሻ ቀን ትንቅንቅ ውስጥ ያለፉበትን ታሪክ አስቀምጠዋል።

ነገስ በ7ኛው ተመሳሳይ ፍልሚያ ማን የበላይ ሆኖ ይጨርስ ይሆን ? ቅዱስ ጊዮርጊስ ዕድሉን በራሱ ወስኖ 15ኛ ክብሩን ይቀዳጅ ይሆን ? ወይስ ፋሲል ከነማ እስከዛሬ ያልታየ ከኋላ የመነሳት ሩጫውን ተከታታይ ክብር በማሳካት ይደመድም ይሆን ?


መልሱን ለማግኘት ነገ ረፋድ 04:00 ላይ መላው የእግርኳሱ ቤተሰብ ዓይኑን ባህር ዳር ላይ ያደርጋል።