“…በዚህ ዓይነት ደረጃ ከፕሪምየር ሊጉ መውረድ ለእኔ ወንጀል ነው…” አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው

ድሬዳዋ ከተማ ፋሲል ከነማን 3-2 ያሸነፈበትን ሂደት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው አምርረው ኮንነዋል።

ዛሬ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊጉን ማሸነፉን ከማረጋገጡ ባለፈ አነጋጋሪ የነበረው ፋሲል ከነማ በድሬዳዋ ከተማ ተሸንፎ አዲስ አበባ ከተማ ሦስተኛ ወራጅ ቡድን መሆኑ የተረጋገጠበት ሂደት ነው። እስከ 77ኛው ደቂቃ ድረስ በፋሲል ከነማ 2-0 መሪነት የቀጠለው ጨዋታ በቀሪ ደቂቃዎች በድሬዳዋ 3-2 አሸናፊነት የመጠናቀቁ ነገር በተለይም አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸውን እና የቡድናቸውን አባላት ሀዘን ውስጥ የከተተ ሆኗል። ይህ ስሜት የተንፀባረቀነት አሰልጣኙ ከሱፐር ስፖርት ጋር ያደረጉት ቆይታም የሚከተለው ነበር።

“መናገር ይከብዳል። እኔ የማዝነው በኢትዮጵያ እግርኳስ ነው። ነገ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዕድገት የተመለከትነው ነገር ተገቢነት የጎደለው ነው። እኔ በጣም ውስጤን ተሰምቶኛል። ምን ውሳኔ እንደሚወሰንም አላውቅም ፤ ይሄ ነገር በዝምታ ከታለፈ ግን ወደ ፊት የኢትዮጵያ ኳስ ላይ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ደረጃ ትልቅ ታሪክ ያለው ቡድን ላይ ? አልተዋጠልኝም።”

“በመጀመሪያው አጋማሽ በጣም ጥሩ ነበርን ፤ ሙከራዎችን አድርገናል ብዙ ኳሶችንም ስተናል። ከዛ ተነጋግረን ከዕረፍት መልስ ከገባን በኋላ ፍፁም ቅጣት ምቱ አውርዶናል። ያ ነገር ነው እኛ ላይ የተከሰተው።”

“እስከ ሰማንያ ምናምነኛው ደቂቃ ድረስ 2-0 ነበሩ። እኛም እዚህ አጥቂዎች እየቀየርን ቶሎ ለመድረስ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። በዚህ ዓይነት ደረጃ ከፕሪምየር ሊጉ መውረድ ለእኔ ወንጀል ነው። በጣም በጣም ያዘንኩነት ቀን ይሄ ቀን ነው።‌‌”