አዲስ አበባ ከተማ ቅሬታ አቀረበ

በመጣበት ዓመት ዳግመኛ ወደ ከፍተኛ ሊጉ እንደወረደ ያረጋገጠው አዲስ አበባ ከተማ ከጨዋታ በፊት ስጋቱን ገልፆ የነበረ ሲሆን ከጨዋታው በኋላ ደግሞ አቤቱታውን አሰምቷል።

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2014 የውድድር ዘመን በዛሬው ዕለት በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወቃል። ከዚህ ውጪ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ረፋድ ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ 4-0 የተሸነፈው አዲስ አበባ ከተማ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱን ተከትሎ ፋሲል ከነማ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ያደረጉት ጨዋታ ከአቅም በታች የተካሄደ ነው በማለት ቅሬታውን ለአወዳዳሪው አካል በደብዳቤ አሰምቷል።

እንደ አዲስ አበባ ከተማ ገለፃ ከሆነ “ የሁለተኛው ዙር ማጠናቀቂያ ፣ የሻምፒዮና እና የወራጅ ቡድኖች መለያ ውድድር በዛሬው ዕለት እንዳይላቀቁ በሚል በዕኩል ሰዓት ሦስት ጨዋታዎች እንዲካሄዱ በተወሰነው መሠረት ጨዋታዎቹ ተካሂደዋል። በፋሲል ከነማ እና በድሬዳዋ ከተማ መካከል በተደረገው ግጥሚያ የፋሲል ቡድን በከፍተኛ ብቃት ባለበት የአሁኑ ደረጃው ለሻምፒዮን እየተፎካከረ ከወራጅ ቀጠና ውስጥ ከሚገኘው ድሬዳዋ ቡድን ጋር ከአቅም በታች በመጫወት በቡድናችን ላይ የመውረድ አደጋ ውስጥ እንድንገባ ያደረገ ከምሆኑም በላይ የውድድሩን ደንብ እና መንፈስ የሚያረክስ ሥራ የፈፀመ መሆኑ ታውቆ፣ በፊልም መረጃ በተደገፈ ምርመራ የሊግ ካምፓኒው በማድረግ ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጥ በአክብሮት እንጠይቃለን።” በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

ከሁለት ቀናት በፊትም አዲስ አበባ ከተማ ሊግ ካምፓኒው ጨዋታዎቹን በተመሳሳይ ሰዓት እንዲደረጉ በመወሰኑ ባመሰገነበት ደብዳቤ በዛሬው የጨዋታ ዕለት ዙሪያ

” ሁሉም ቡድኖች በሙሉ አቅም መጫወታቸውን የሚከታተል ቡድን እንዲቋቋም እና በሜዳ ላይ ብቃት ብቻ እንዲለይ እየጠየቅን ከሜዳ ውጪ ውጤትን ለመወሰን እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች የበርካታ ስፖርት ቤተሰብ ልብ መሳብ የቻለውን ሊግ ለቀጣይ ዓመታት ይሄንን ግለት ይዞ ለመቀጠል የማያስችል እና ለስፖርቱ ዕድገት ድጋፍ እያደረገ ያለውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን የማያበረታታ በመሆኑ በእናንተ በኩል ከጨዋታ በፊትም ሆነ ጨዋታው በሚካሄድበት ጊዜ ከዚህ በፊት በነበረው ድጋፍ እና ክትትላችሁ በተሻለ ቁጥጥር በማድረግ ክፍተት በሚፈጥሩት ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ከወዲሁ በጥብቅ ለማሳሰብ እንወዳለን። ” በማለት ያለውን ስጋት ጠቁሞ ነበር።