ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ ፣ መከላከያ እና አዲስ አበባ ከተማ ወሳኝ ድል አሳክተዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በተደረጉ ሦስት መርሀግብሮች ሲጀመሩ ሀዋሳ ከተማ ቦሌን ፣ መከላከያ ቅዱስ ጊዮርጊስን ፣ አዲስ አበባ ከተማ ጌዲኦ ዲላን በማሸነፍ ሦስት ነጥብ አግኝተዋል፡፡

ሀዋሳ ከተማ 2-1 ቦሌ ክፍለ ከተማ

ረፋድ 3፡00 ሰዓት ሲል የአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የዕለቱ የመጀመሪያ የሆነው የሀዋሳ ከተማ እና ቦሌ ክፍለከተማን ጨዋታን አስተናግዷል፡፡ የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻለ መስለው መታየት የቻሉት የአሰልጣኝ ቻለው ለሜቻው ቦሌ ክፍለ ከተማ ቢሆንም በሂደት በመስመር አጨዋወት የተሻለ ጥቃት የመሰንዘር ወጥነት ሲያሳዩ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች ወደ ጎል በተጠጉበት ቅፅበት የመጀመሪያ ጎላቸውን አግኝተዋል፡፡ 12ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ማዕደር ባዬ ወደ ግብ ክልል ስታሻማ ኳስ በእጅ መነካቱን ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ዙፋን ደፈርሻ ከመረብ አሳርፋ ሀዋሳን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡ ከአንድ ደቂቃ ቆይታ በኋላ ረድኤት አስረሳኸኝ ወደ ጎል የመታችውን ኳስ የቦሌዋ ተከላካይ ቃልኪዳን ንቅበሸዋ ለማውጣት ስትሞክር በራሷ መረብ ላይ አሳርፋው ሀዋሳን ወደ 2-0 በማሸጋገር ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ሀዋሳዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተቀዛቀዘ መልኩ መንቀሳቀስ ሲችሉ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ንግስት በቀለ አድልቶ በመጫወት ቦሌዎች ብልጫን ለመውሰድ ጥረት አድርገዋል፡፡ በዚህም 47ኛው ደቂቃ ላይ ስንታየው ኢርኮ ቦሌን ወደ ጨዋታ የምትመልስ ጎል ከመረብ ብታሳርፍም በቀሩት ደቂቃዎች ተጨማሪ ጎልን መመልከት ሳንችል ጨዋታው 2-1 በሀዋሳ አሸናፊነት ፍፃሜን አግኝቷል፡፡

መከላከያ 3-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ

በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ከሚባሉ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው መከላከያ ከቀትር በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን ገጥሞ የ3-0 ድል ተቀናጅቷል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊሶች የብስለት ችግር ተንፀባርቆ መታየት በቻለበት እና የመከላከያ የአጥቂ ክፍል በተሻለ ጥቃት መሰንዘር በቻለበት በሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ፈረሰኞቹ እንስቶች በተደጋጋሚ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ ቢችሉም ያገኙትን በአግባቡ የተጠቀሙት ግን መከላከያዎች ናቸው፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ 12ተኛው ደቂቃ ላይ በግምት ከአርባ ሜትር ላይ የተሰጠውን የቅጣት ምት መሳይ ተመስገን ወደ ጎል በቀጥታ ስትመታው የግብ ጠባቂዋ በረከት ዘመድኩን የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ታክሎበት መከላከያ ቀዳሚ ሆኗል፡፡

ከዕረፍት ሲመለሱ ሁለቱ ቡይኖች አሁንም የመከላከያ የተሻለ የማጥቃት ሀይልን ማስተዋል የቻልነበት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ 55ተኛው ደቂቃ ላይ የጊዮርጊሶች የመከላከል ድክመትን ተመልክታ መሳይ ተመስገን ድንቅ ጎል ለራሷ እና ለክለቧ በማስቆጠር 2ለ0 አድርጋለች፡፡ 73ኛው ደቂቃ ላይ በተደጋጋሚ በየሳምንቱ ግቦችን እያስቆጠረች የምትገኘው ረሂማ ዘርጋው ሶስተኛ ጎል በማከል ጨዋታው በመከላከያ 3ለ0 የበላይነት ተደምድሟል፡፡

ጌዲኦ ዲላ 0-3 አዲስ አበባ ከተማ

በተደጋጋሚ ነጥብ ሲጥል የሰነበተው አዲስ አበባ ከተማ የዛሬውን ጨዋታ 3-0 ድል ተወጥቶ ወደ አሸናፊነት መንፈስ ተመልሷል፡፡

የጌዲኦ ዲላ ደካማ የጨዋታ አቀራረብን ባየንበት እና በተቃራኒው የአዲስ አበባ የአጥቂ ክፍል ከወትሮው ተሻሽሎ በታየበት ጨዋታ አሪያት ኦዶንግ 44ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረችው ጎል የመዲናይቱን ክለብ መሪ አድርጋለች፡፡ ጨዋታው ቀጥሎ ወጥ የማጥቂያ መንገዳቸው የተዘበራረቀ ቢመስልም የጌዲኦ ዲላን ደካማ የተከላካይ ክፍል ለመስበር ያልተቸገሩት አዲስ አበባዎች ከዕረፍት መልስ በቤተልሄም ሰማን እና በአንጋፋዋ አማካይ ትርሲት መገርሳ ተጨማሪ ግቦችን አግኝተው ጨዋታው 3ለ0 ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡