“ሥራችንን በሚገባ ሰርተን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ይሄንን ዋንጫ አበርክተናል” አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአራት ዓመታት በኋላ የሊጉን ዋንጫ እንዲያገኝ ያስቻሉት አሠልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ከፌሽታው ስሜት ሳይወጡ ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

ስለውድድሩ 

“ሠላሳ ጨዋታዎች አድርገናል። ሠላሳውም ጨዋታ ለእኛ የዋንጫ ያህል ነበር። ጠንካራ ጨዋታዎች ነበሩ። በዚህ አጋጣሚ ሁሉም ቡድን ከእኛ ጋር ሲጫወት የሚያሳየውን ነገር ሁሌ ቢጫወት የሀገራችን እግር ኳስ በጣም ከፍ ይላል። ዞሮ ዞሮ ሠላሳውም ጨዋታ ለእኛ ከባድ ጨዋታ ነው። ጭንቀታችንን ይዘን ተጫዋቾቹን አበረታተን የተሻለ ቦታ እንዲደርሱ ለማድረግ ሞክረናል።

በውድድሩ ስለገጠማቸው ፈተና

“ሻምፒዮን እንዳትሆን ብዙ መሰናክሎች አሉ። ከአዳማ ስንመጣ ብዙ ተጫዋቾቻችን ተጎድተው ነበር። ባህር ዳር ስንመጣ ያገግማሉ ብለን ነበር። በዚህ ሂደት ውስጥ ሁሉንም ማግኘት አልቻልንም። ፈጣሪ ይመስገን እንደምንም ቡድኑን እያደራጀን እዚህ ደርሰናል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ታላቅነት ለማሳየት ከ30 ጨዋታዎች አንድ ጨዋታ ብቻ ነው የተሸነፈው። በአጠቃላይ ሁሉም ጨዋታዎች ጠንካራ ነበሩ።

በመጨረሻ ሰዓት ውጥረት ውስጥ ስለመግባታቸው

“ይህ እግር ኳስ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌላም ሀገር ያለ ነው። ያሉትን ነገሮች ተቆጣጥረህ ነው መሄድ ያለብህ። ሁሉም ቡድን ከእኛ ጋር ለመጫወት ሲመጣ ትኩረት ሰጥቶ ነው። እንደዚህ አይነት ነገሮች ጫና ያመጣሉ ፤ በዚህ ውስጥ አልፈን የተሻለ ውጤት አምጥተን ዋንጫውን አንስተናል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች እና የስፖርት ወዳጆች የዘንድሮ ውድድር ፉክክር የበዛበት ሆኖ ተከታትለውታል። ይህንን ላደረጉት የሊጉ አዘጋጆች ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ።

በተጫዋችነት እና አሠልጣኝነት ስላገኘው ዋንጫ

“ትልቅ ስሜት አለው። እውነቱን ስነግራችሁ መጫወት ይበልጣል። ከማሰልጠን መጫወት ይሻላል። ማሰልጠን ብዙ ነገሮች አሉት። ስትጫወት ራስህን ነፃ አድርገህ ነው ፤ ስታሰለጥን ግን ብዙ ነገሮችን ተሸክመህ ነው። እኔ በሁለቱም ነገሮች ሁሉንም ነገር አሳክቼ እዚህ በመድረሴ በጣም ደስተኛ ነኝ።

ዋና አሠልጣኙ ከተነሱ በኋላ ስለነበረው የቡድኑ ጉዞ

“ቡድኑ ውስጥ ብቃት እና አቅም ያላቸው ታላላቅ ተጫዋቾች አሉ። ከወጣቶቹ ጀምሮ አቅም አላቸው። ይሄንን ተቆጣጥረን በራስ መተማመናቸውን ማሳደግ ላይ ነበር የሰራነው። ይሄ ተሳክቶልን ለዚህ ውጤት በቅተናል።

ከ4 ዓመት በኋላ ወደ ዋንጫ ስለመጡበት መንገድ

“የክለቡ አመራሮችም ሆነ ደጋፊው ዋንጫ ይፈልጋል። ቡድኑ ሁሌ ዋንጫ የሚያገኝ ነው። ቡድኑ ያለፉትን ሦሰት እና አራት ዓመታት በብዙ ሂደት ተጫዋቾች ሲቀያየሩ ሽግግር ላይ የነበረ ነበር። አሁን ግን ያለው ስብስብ አቅም እንዳለው እናውቅ ነበር። ስራችንን በሚገባ ሰርተን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ይሄንን ዋንጫ አበርክተናል።”