የ2014 ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ፍፃሜውን አግኝቷል

መርሐ-ግብር ለማሟያ እና ለክብር ብቻ በተደረጉት ሦስት የዛሬ ጨዋታዎች መከላከያ ጅማን ድል ሲያደርግ ሲዳማ ከሀዲያ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ከባህር ዳር አቻ ተለያይተዋል።

ረፋድ 4 ሰዓት በተደረገው ጨዋታ መከላከያ ሦስት ነጥቦች አግኝቶ ሦስት ደረጃዎችን ያሻሻለበትን ውጤት አሳክቷል። የጦሩ ብቸኛ ግብ 24ኛው ደቂቃ ላይ ገናናው ረጋሳ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ አዲሱ አቱላ በሚገርም አጨራረስ አስቆጥሯል። ሁለቱ ቡድኖች እረፍት ሊወጡ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ዳዊት ፍቃዱ ከመሐመድኑር ናስር የተቀበለውን ኳስ ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽሮበታል። በሁለተኛው አጋማሽ ከሙከራዎች የራቀው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት ቀርቷል።

7፡00 ላይ የሲዳማ ቡና እና የሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ ሲደረግ ጨዋታው ገና በተጀመረ በ3ኛው ደቂቃ ይገዙ ቦጋለ ባስቆጠራት ግብ ሲዳማዎችን መሪ ሆነዋል። ወደ ጨዋታው ለመመለስ የጣሩት ሀዲያዎች 23ኛው ደቂቃ ላይ ዑመድ ኡኩሪ ወደግብ የሞከረውን ኳስ ግብጠባቂው በሚገርም ሁኔታ መልሶታል። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ራምኬል ሎክ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ የቀኙን ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል። በተጨማሪም በ32ኛው ደቂቃ ዑመድ ኡኩሪ ከግራ መስመር ወደግብ የሞከረው ኳስ ዒላማውን ስቷል። 38ኛው ደቂቃ ላይ ግን ራምኬል ሎክ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን አቻ አድርጓል።

ከእረፍት መልስ ይገዙ ቦጋለ ብቻውን ግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም ትልቅ የግብ እድል አባክኗል። በአንድ ደቂቃ ልዩነት ከመልሶ ማጥቃት ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ የተገናኘው ዑመድ ኡክሪ ዒላማውን ባለመጠበቁ ኳሱ የግራውን ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል። 70ኛው ደቂቃ ላይ የሀዲያ ሆሳዕናው ግብ ጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳ ለማቀበል ሲሞክር በሠራው ስህተት ኳሱን ተደርቦ ማስቀረት የቻለው ይገዙ ቦጋለ በቀላሉ አስቆጥሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል። 83ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ተቀይሮ የገባው ባዬ ገዛኸኝ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን አቻ አድርጎ ጨዋታው ተገባዷል።  ሲዳማ ቡናም ውድድሩን ሦስተኛ ሆኖ በማጠናቀቁ የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።

10፡00 ላይ በኢትዮጵያ ቡና እና ባህር ዳር ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ 6ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ደረሰ ከሳጥን ውጪ ወደግብ ሞክሮት ግብ ጠባቂው በሚገርም ብቃት ወደ ማዕዘን ባስወጣው ኳስ የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አስተናግዷል። በ3 ደቂቃዎች ልዩነት ማውሊ አመቻችቶ ባቀበለው ኳስ ግብጠባቂ ጋር የተገናኘው ተመስገን ደረሰ ወደግብ ሞክሮ ግብጠባቂው ሲመልስበት በድጋሚ አግኝቶ ቢሞክርም ስዩም ተስፋዬ አውጥቶበታል።

20ኛው ደቂቃ ላይ ገዛኸኝ ደሳለኝ አለልኝ አዘነ ላይ በሠራው ጥፋት ባህር ዳሮች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምትም ኦሴ ማውሊ ግብ አድርጎታል። ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ዘለግ ያሉ ደቂቃዎች ቢወስድባቸውም በ66ኛው ደቂቃ አቤል ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ቁመታሙ አማካይ አብነት ደምሴ አስቆጥሮት አቻ ሆነዋል። የውድድር ዓመቱ የመጨረሻ ጨዋታም በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።