የ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ተራዝሟል

በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት በቀጣዩ ዓመት እንዲከናወን ቀጠሮ የተያዘለት የአፍሪካ ዋንጫ በወራት መገፋቱ ከደቂቃዎች በፊት ይፋ ሆኗል።

ቀጣዩ የአህጉራችን ትልቁ የብሔራዊ ቡድኖች ውድድር በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር አይቮሪኮስት አዘጋጅነት እንደሚከናወን ይታወቃል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ጨምሮ ሌሎች ቡድኖችም በዚህ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የምድብ ማጣሪያ ፍልሚያቸውን እያደረጉ ይገኛሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሁኑ ሰዓት በሞሮኮ ራባት የካፍ የሥራ-አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ውድድሩ በወራት እንዲገፋ መወሰናቸው ተሰምቷል።

ውድድሩ እንዲገፋ የሆነበት ምክንያት ደግሞ በአይቮሪኮስት በሰኔ እና ሀምሌ የክረምት ወቅት ስለሆነ ነው ተብሏል። በአሁኑ ሰዓትም በሀገሪቷ የተለያዩ ከተሞች ከፍተኛ ዝናብ እየዘነበ የጎርፍ አደጋዎች መበርከታቸው ተገልጿል። ይህንን ተከትሎ ከሰኔ 15 2015 እስከ ሀምሌ 16 2015 እንዲደረግ ቀጠሮ የተያዘለት ትልቁ የሀገራት ውድድር ወደ ጥር 2016 መገፋቱ ተረጋግጧል።

በካሜሩን አስተናጋጅነት የተከናወነው የቀደመው ውድድር በ2021 ይደረጋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም በኮቪድ-19 ምክንያት ተግፍቶ ከወራት በፊት መከናወኑ ይታወሳል።