የሴቶች ፕሪምየር ሊግ| ሀዋሳ ወደ መሪው የሚጠጋበትን ነጥብ ሲጥል ጊዮርጊስ እና አዲስ አበባ አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ጅማሮውን አድርጎ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዲስ አበባ ከተማ ሲያሸንፉ ሀዋሳ ከአዳማ ጋር አቻ ተለያይቶ ወደ መሪው ንግድ ባንክ የሚጠጋበትን ዕድል አምክኗል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 ጌዲኦ ዲላ

በአዳማ ከተማ እየተደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ2014 የውድድር ዘመን 19ኛ ሳምንት ላይ የደረሰ ሲሆን የሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታም በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጌዲኦ ዲላ መካከል ተከናውኗል።

ዝናባማ በሆነ እና ኳስን ለመጫወት እጅጉን አስቸጋሪ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አብዛኛዎቹን የጨዋታ ደቂቃዎች ሜዳው ጭቃማ መሆኑን ተከትሎ ረጃጅም ኳሶችን የተመለከትን ሲሆን 23ኛው ደቂቃ ላይ የጌዲኦ ዲላን የተከላካይ መስመር ስህተት በአግባቡ የተጠቀመችው አጥቂዋ እየሩስ ወንድሙ ያስቆጠረቻት ብቸኛ ጎል ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸናፊ አድርጋለች፡፡

አዲስ አበባ ከተማ 1-0 ቦሌ ክፍለከተማ

ከማለዳው ዝናብ መለስ ብሎ ፀሀያማ የአየር ባህሪን ተላብሶ ከቀትር በኋላ የሁለቱን የመዲናይቱ ክለቦችን ያገናኘው ጨዋታ በአዲስ አበባ ከተማ የበላይነት ተጠናቋል፡፡ በሜዳ ላይ ጠንካራ ፉክክርን ባየንበት እና በአንድ ሁለት ቅብብል ቦሌዎች በእንቅስቃሴ ብልጫ ቢያሳዩም በረጃጅም ተሻጋሪ ኳሶች ወደ አጥቂዎቹ ቤተልሄም ሰማን እና አሪያት ኦዶንግ በመጣል ለመጫወት የታተሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ተሳክቶላቸው ባገኟት አንድ ግብ አሸናፊ ሆነዋል፡፡

52ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር በኩል በሻዱ ረጋሳ መሬት ለመሬት ወደ ግብ ክልል ያሻገረችውን ኳስ አሪያት ኦዶንግ ከመረብ አሳርፋው አዲስ አበባን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡ ተጫዋቿ ግቡን ካስቆጠረች በኋላ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ቆይታዋ ላሰለጠናት እና በአሁኑ ሰዓት የቦሌ አሰልጣኝ ለሆነው ቻለው ለሜቻ ክብር ስትል ደስታዋን ሳትገልፅ ቀርታለች፡፡ ጨዋታውም በአዲስ አበባ ከተማ 1ለ0 ድል ተጠናቋል፡፡

ሀዋሳ ከተማ 0-0 አዳማ ከተማ

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ እና አዳማ ከተማ መካከል ተከውኗል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የሴቶች ልማት እና ውድድር ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙ ተገኝተው በተከታተሉት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ወደ መሪው ንግድ ባንክ የሚጠጋበትን ዕድል አምክኗል፡፡ በሙሉ የጨዋታው ደቂቃ ሀዋሳ ከተማ የአጥቂ መስመሩን አብዝቶ በመግባት ጎል አስቆጥሮ ለማሸነፍ ብርቱ ፉክክርን ማሳየት ቢችልም አዳማ ከተማ ከወትሮ ተሽሎ ጠንካራ የሜዳ ላይ ተፎካካሪ ሆኖ በመቅረብ ጨዋታው ያለ ጎል 0ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ያጋሩ