ለወራት በመደበኛ ፍርድ ቤት ሲታይ የቆየው የሀድያ ሆሳዕና እና የሰባት ተጫዋቾች ክስ ጉዳይ በመጨረሻም ውሳኔ አግኝቷል።
በ2013 የውድድር ዘመን ለሀዲያ ሆሳዕና ሲጫወቱ የቆዩት አማኑኤል ጎበና፣ ሱሌይማን ሀሚዲ፣ ብሩክ ቃልቦሬ፣ አዲስ ህንፃ፣ ደረጄ ዓለሙ፣ አክሊሉ አያናው እና ተስፋዬ በቀለ ከክለቡ ጋር በተስማሙት መሠረት በቼክ የተቀበሉት በድምሩ 2.57 ሚልዮን ብር አልተከፈለንም በማለት ከስድስት ወር በፊት ጉዳያቸውን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት በመውሰድ ክስ መመስረታቸውን ይታወቃል። የሰው ምስክሮች እና የሰነድ ማስረጃዎችን ከመመልከቱ አስቀድሞ ፍርድ ቤቱ ሀዲያ ሆሳዕና ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ከሚያገኘው የገቢ ክፍፍል ላይ በአጠቃላይ 2.57 ሚልዮን ብር ታግዶበት እንዲቆይ ውሳኔ አሳልፎ መቆየቱም ይታወሳል።
በስተመጨረሻም የተጫዋቾቹን ጉዳይ የያዙት የህግ አማካሪ እና ጠበቃ አቶ ብርሐኑ በጋሻው እንዳደረሱን መረጃ ከሆነ ክሱን ሲመረምር የቆየው የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምድብ 2 ችሎት የሰነድ እና የሰው ምስክሮችን ካዳመጠ በኋላ ተከሳሽ ሀዲያ ሆሳዕና ክለብ ለሰባቱ ተጫዋቾች በቼክ ያልከፈለው ገንዘብ ጨምሮ ሌሎች ወጪዎችን ታሳቢ በማድረግ በድምሩ 3.6 ሚሊየን ብር (ወለድን ሳይጨምር) እንዲከፍል ወስኗል።
ሀድያ ሆሳዕና ይግባኝ ለመጠየቅ ከፈለገ መዝገቡ ተገልብጦ ለይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት እንዲላክ መያያዙም ታውቋል።