የዋልያዎቹ ተጋጣሚ ዝግጅቷን ጀምራለች

በቻን ማጣሪያ ከኢትዮጵያ ጋር የምትፋለመው ደቡብ ሱዳን በትናንትናው ዕለት ዝግጅቷን ጀምራለች።

በሀገር ውስጥ ሊግ ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የቻን ውድድር በቀጣዩ ዓመት በአልጄሪያ እንደሚከናወን ይታወቃል። በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ብሔራዊ ቡድኖችን ለመለየት ደግሞ ከቀናት በኋላ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች የሚጀምሩ ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያም የመጀመሪያ ማጣሪያዋን ከደቡብ ሱዳን ጋር ታከናውናለች።

ሐምሌ 14 እና 24 ታንዛኒያ ላይ ለሚደረጉት ጨዋታዎች የዋልያዎቹ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በትናንትናው ዕለት ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ማስተላለፋቸው እና በቀጣዩ ሳምንት መጀመሪያ ዝግጅት ለመጀመር ማሰባቸው መገለፁ ይታወቃል። በተቃራኒው ተጋጣሚያችን ደቡብ ሱዳን ደግሞ በትናንትናው ዕለት ዝግጅት መጀመሯ ተሰምቷል።

በቡሉክ ሜዳ 26 ተጫዋቾችን በመያዝ ልምምድ የጀመረው ቡድኑ ከኢትዮጵያ ጋር ጨዋታውን ከማድረጉ በፊት የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ እንደያዘ ተጠቁሟል። ጁባ ላይ መቀመጫቸውን ያደረጉ በርካታ ተጫዋቾች የሚገኙበት ስብስቡ ምናልባት በቀጣዮቹ ቀናት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ሊያካትት እንደሚችል ተገልጿል።