የእግርኳስ ህይወቱን ጉዳት እየፈተነው የሚገኘው ሐብታሙ ወልዴ የመኪና ተሸላሚ ሆኗል።
በጅማ አጋሮ የተወለደው ሐብታሙ ወልዴ ከትውልድ አካባቢው የጀመረው የእግርኳስ ህይወቱ በክለብ ደረጃ በኒያላ በመቀጠል በኢትዮጵያ መድን በነበረው የሁለት ዓመት ስኬታማ ቆይታ መነሻነት ወልድያ እና ድሬዳዋ ከተማ ተጫዋቹን ለማስፈረም ውዝግብ ቢፈጥሩም በስተመጨረሻም በ2009 ድሬዳዋ ከተማን በመቀላቀል ለሦስት ዓመት ጥሩ ቆይታ አድርጓ። በማስከተል ወደ መከላከያ በማምራት ሲጫወት ቆይቶ ወደ አዳማ ከተማ ካቀና በኋላ ያለፉትን አንድ ዓመታት በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ዕርቆ ይገኛል።
አሁን ከሜዳ ርቆ የቆየው አጥቂው ሐብታሙ ወልዴ በሌላ ስኬት ከሰሞኑን ብቅ ብሏል። በጅማ ከተማ የአዋሽ ባንክ ደንበኛ በመሆን ከአራት ዓመት በፊት ቁጠባ የጀመረው ተጫዋቹ ይቆጥቡ፣ይቀበሉ፣ ይሸለሙ የሎተሪ ዕጣ ደርሶት የመኪና አሸናፊ ሆኗል። ከሰሞኑን በተዘጋጀው የሽልማት መርሐ-ግብር ላይ ተጫዋች የአይሱዚ የጭነት ተሽከርካሪ መኪና ተሸላሚ በመሆን ቁልፉን መረከቡ ታውቋል። ሶከር ኢትዮጵያም ከሐብታሙ ወልዴ ጋር ሽልማቱን በተመለከተ አጭር ቆይታ አድርጋለች።
“መቆጠብ ከጀመርኩኝ አራት ዓመት ሆኖኛል ፤ እንደአጋጣሚ ከወራት በፊት በተዘጋጀው የይቆጥቡ ይሸለሙ ዕድል የሎተሪ ዕጣውን ወስጄ ድንገት በተቀመጥኩበት ተደውሎ የአይሱዚ መኪና ተሸላሚ መሆኔ ተነገረኝ። በጊዜው አላመንኩም ነበር። በኋላ እውነት መሆኑን አረጋግጬ ከቀናት በፊት በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ የመኪና ቁልፉን ተረክቤአለው።
“ሽልማቱን በማግኘቴ በጣም ደስ ብሎኛል። በተለይ ለተጫዋቾች መቆጠብ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ምሳሌ እንደምሆን ሳስብ የበለጠ ደስታ ይሰማኛል። ብዙም በእግርኳሱ አካባቢ እንዲህ ያለ ነገር አልተለመደም። እኔ የመጀመሪያም ሳልሆን አልቀርም። አሁን መኪናውን ተረክቤ የጭነት ስራ እየሰራሁበት ነው። እግርኳስ በጣም ነው የምወደው ፤ ሆኖም ያለፉትን ሁለት ዓመታት ጉዳት እንደፈኩት ሊያጫውተኝ አልቻለም። አሁን ከጉዳቴ ደህና በመሆኔ በቀጣይ ዓመት ወደ እግርኳሱ ብቅ ብዬ ለመጫወት ልምምዶችን እየሰራው እገኛለው።”