ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2014 ኮከቦቹን በሸራተን አዲስ ሆቴል ዛሬ አመሻሹን ይሸልማል፡፡ ከሽልማት ስነ ሥርዓቱ አስቀድሞ የፕሪምየር ሊጉ አክሲዮን ማኅበር ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ተነስቶላቸዋል። በዋናነት ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል ዋና ዋናዎቹን በተከታዩ መልክ አቅርበንላችኋል፡፡
በቀጣዩ ዓመትም ውድድሩ በተመረጡ ሜዳዎች ስለመደረጉ
“በሚቀጥለው ዓመት ሊጉን በጊዜ ለመጀመር አስበናል፡፡ የተቀመጠውን መለኪያ ያለፉ ስታዲየሞች ፣ የተቀመጡትን መስፈርት ያሟሉ ሆቴሎች ፣ በተጨማሪም መለኪያውን ያለፉ የልምምድ ሜዳዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ከምንም በላይ ፀጥታው የተጠበቀ አካባቢን ነው የምንፈልገው ስለዚህ እነዚህ ባሟሉ ቦታዎች በጀመርነው ፎርማት ውድድራችንን እንቀጥላለን፡፡
በመጨረሻ ጨዋታዎች ስለነበረው የጨዋታ መላቀቅ ቅሬታ
ገና ነው አላለቀም፡፡ ማች ፊክሲንግን ለማጣራት እና ዕርምጃ ለመውሰድ ረጅም ጊዜ ነው የሚፈጀው ፤ እውነቱ እስኪታወቅ ድረስ። ታውቃላችሁ ጣሊያን ውስጥ የተፈጠረውን ፤ የጣልያን ፌዴሬሽን አይደለም ያጋለጠው ፤ አንድ ጋዜጠኛ ነው ማስረጃዎችን አውጥቶ ክለቦች እንደዲቀጡ ያደረገው። እኛም ሀገር እንደዚህ አይነት ሁኔታ መከሰቱን ጥርጣሬ ውስጥ የሚጥሉ ነገሮች አሉ። ነገር ግን እነኚህን ጥርጣሬዎች በህግ እና በደንብ ተቀብለህ በጥርጣሬ ብቻ እርምጃ አትወስድባቸውም። ለማንኛውም ሁለት ነገር አለ፡፡ ይሄ አሁን ያለው ሁኔታ በቻልነው መጠን ለማጣራት እንሞክራለን፡፡ ሁለተኛ ከዚህ ሂደት ተነስን የሚቀጥለው ዓመት ምን እናድርግ ፤ ደንባችን ውስጥ ምን እንክተት ፤ ምን አይነት ህግ እንቅረፅ የሚለውን እናደርጋለን፡፡ ስለዚህ በሚቀጥለው ዓመት እኔ ሳስበው አሁን አስራ አራተኛ ፣ አስራ አምስተኛ እና አስራ ስድስተኛ ወጥታችዋል እናንተ ትወርዳላችሁ የሚለው ብቻ አያስኬድም። ወደፊት ወራጆች እንዴት ይውረዱ የሚለው እጅግ አሳሳቢ ጥያቄ ነው፡፡ እሱን በቀጣይ በህግ አጥብቀን ተቀባይነት ሲያገኝ ወደ ራሳችን ጠቅላላ ጉባኤ አቅርበን ደንባችን ውስጥ አካተን በዛ እንቀጥላለን ማለት ነው፡፡
በቀን ስለተደረጉ ጨዋታዎች
“ባለን ተጨባጭ ሁኔታ ስታዲየሞቻችን መብራት ቢኖራቸው የአካባቢው ሁኔታ የተረጋጋ ፀጥታ ቢኖረው በማታ ማጫወትን እንመርጣለን፡፡ ነገር ግን አብዛኛዎቹ ስታዲየሞቻችን የማታ መብራት የላቸውም በተለይ የባህርዳር ከዛም አልፎ ደግሞ መብራት እንኳን ቢኖርም ደግሞ ተመልካቹ ህዝብ አምሽቶ ጨዋታ ቢያይ ምን አይነት የደህንነት ሁኔታ የተረጋገጠ ነገር አለ የሚለው ለእኛ የለም። ስለዚህ ከእነኚህ ከእነኚህ ሁኔታዎች ተነስተን ውድድሩ አራት ሰዓት እና ሰባት ሰዓት መርጠናል። ሌላ ምንም አማራጭ የለንም፡፡