ዛሬ በይፋ በተጀመረው የዝውውር መስኮት ተሳታፊ የሆነው ኢትዮጵያ ቡና ወጣቱን አማካይ አስፈርሟል።
ከአሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ ጋር በይፋ የተለያየው ኢትዮጵያ ቡና አዲሱን የቡድኑን አሰልጣኝ በቅርቡ ይፋ ከማድረጉ አስቀድሞ በዛሬው ዕለት ኃይለሚካኤል አደፍረስ እና አብዱልሀፊዝ ቶፊቅን ረፋድ ላይ ከሰበታ ከተማ ለሦስት ዓመት ማስፈረሙን ይፋ አድርጎ ነበር። አሁን ከሰዓታት በኋላ ክለቡ ይፋ ያደርገዋል ተብሎ የሚጠበቀው ሦስተኛው ፈራሚ ደግሞ አማካዩ አብዱልከሪም ወርቁ ይሆናል።
በኢትዮጵያ መድን ከታዳጊ ቡድን አንስቶ እስከ ዋናው ቡድን በመጫወት የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው ወጣቱ አማካኝ አብዱልከሪም ወርቁ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በወልቂጤ ከተማ ስኬታማ ጊዜ አሳልፏል። ለሦስት ዓመት የሚያቆይ ውል ያስራል ተብሎ የሚጠበቀው አብዱልከሪም በኢትዮጵያ ቡና የተሳኩ ዓመታትን ያሳልፋል ተብሎ ይገመታል።
ውል ካላቸው ተጫዋቾች ጋር በስምምነት እየተለያየ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና በቀጣይ ቀናት ተጨማሪ ተጫዋቾችን እንደሚያስፈርም ይጠበቃል።