ሊዲያ ታፈሰ በአፍሪካ ዋንጫ ነገ የሚደረገውን ተጠባቂ ጨዋታ ትመራለች

ኢትዮጵያዊቷ አርቢትር ሊዲያ ታፈሰ በእንስቶች የአፍሪካ ዋንጫ ነገ ምሽት የሚከናወነውን ወሳኝ ጨዋታ እንድትመራ ተመርጣለች።

የ2022 የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል። አስራ ሁለት ሀገራት በሦስት ምድብ ተከፋፍለው የሚያደርጉት ፍልሚያ ከዛሬ ጀምሮ የምድብ የመጨረሻ መርሐ-ግብሮች የሚደረጉበት ሲሆን በምድብ ሁለት በካሜሩን እና ታንዛኒያ መካከል የሚደረገውን ጨዋታ ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ አልቢትር በዋና ዳኝነት እንደምትመራው ታውቋል።

ነገ ምሽት 5 ሰዓት በካዛብላንካ ኮምፕሌክስ ሞሀመድ ስታዲየም የሚደረገው ጨዋታ በአንድ ነጥብ ተበላልጠው የምድቡ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ለሆኑት ቱኒዚያ እና ካሜሩን እጅግ ወሳኝ ነው። ይህንን ተጠባቂ ጨዋታ ሊዲያ ሞሮኳዊቷን ፋቲያ ጄርሞሚ እና ከዲሞክራቲክ ኮንጎ የመጣችው ሚሪሌ ካንጂንጋን ረዳት እንዲሁም የኢሲዋቲኒ ዜግነት ያላትን ሌቲካ አንቶኔላን አራተኛ ዳኛ አድርግ እንድትመራ ካፍ ምደባ ማከናወኑን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።

ሊዲያ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ካሜሩን እና ዛምቢያ ያደረጉትን ጨዋታ በአራተኛ ዳኝነት እንድትመራ ተመድባ የነበረ ቢሆንም የጨዋታው ዋና ዳኛ 58ኛው ደቂቃ ላይ ተጎድታ ቀይራት ገብታ ጨዋታውን በመሐል አልቢትርነት ጨርሳ ነበር።