ከተለያዩ ተጫዋቾች ጋር በስምምነት እየተለያየ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና በተጨማሪ ከቀኝ መስመር ተከላካዩ ጋር በተመሳሳይ ውሳኔ ሊለያይ መሆኑን ተጫዋቹ አረጋግጦልናል።
ከሰሞኑ የዝውውር መስኮቱ መከፍቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ለቀጣይ ዓመት ራሱን አጠናክሮ ለመቅረብ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። በይፋ ወደ ክለቡ የቀላቀላቸው ሁለት ተጫዋቾችን ቢሆንም በቀጣይ በርከት ያሉ ተጫዋቾች ወደ ያስፈርማል ተብሎም ይጠበቃል። ቡናማዎቹ እስካሁን ከታፈሰ ሰለሞን ፣ ሚኪያስ መኮንን ፣ ቴዎድሮስ በቀለ እና ዊልያስ ሰለሞን ጋር በስምምነት መለያየታቸውን ተጫዋቾቹ ለዝግጅት ክፍላችን በገለፁት መሠረት ዘገባ መስራታችን ይታወቃል። ዛሬም ደግሞ ቀሪ የውል ዘመን ካላቸው ተጫዋች መካከል አንዱ ከሆነው ኃይሌ ገብረትንሳይ ጋር በስምምነት የመለያየቱ ነገር እርግጥ መሆኑን አውቀናል።
ከኢትዮጵያ ቡና የታችኛው ቡድን የተገኘው ኃይሌ ከ2010 ጀምሮ ወደ ዋናው ቡድን በማደግ ያለፉትን አራት ዓመታት ሲያገለግል ቆይቷል። የቀኝ መስመር ተከላካዩ ኃይሌ ገብረትንሳይ ከቡናማዎቹ ጋር የሚያቆየው ቀሪ የሦስት ዓመት የውል ዘመን ቢቀረውም በስምምነት ለመለያየት መስማማቱን ራሱ ተጫዋቹ ለዝግጅት ክፍላችን የገለፀ ሲሆን በቀጣይ የስራ ቀን በፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት በመገኘት ከክለቡ ጋር ያለውን ውል እንደሚቀድ ጨምሮ አስረድቷል።