የሊጉ አክሲዮን ማህበር ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተላልፎለታል

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፍትሐ ብሔር ምድብ ችሎት ለሊጉ አክስዮን ማህበር በሀዲያ ሆሳዕና ጉዳይ የትዕዛዝ ውሳኔ አስተላልፏል።

የቀድሞ የሀድያ ሆሳዕና ተጫዋች የነበረው አብዱልሰመድ ዓሊ ክለቡ ሊከፍለኝ የሚገባው በቼክ የተሰጠኝ ብር አልተከፈለኝም በማለት ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት በመውሰድ ሲከራከር ቆይቶ ፍርድ ቤቱ ታህሳስ ወር በዋለው ችሎት የሊጉ አክስዮን ማህበር በዓመቱ መጨረሻ ለሀድያ ሆሳዕና ከሚከፍለው ሂሳብ ላይ የተጠቀሰውን መጠን እንዲታገድ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር።

አብዱልሰመድ ከወራት በፊት በፍርድ ቤቱ ያስተላለፈልኝ ትዕዛዝ ተግባራዊ አልሆነም በማለት በጠበቃው አቶ ብርሀኑ በጋሻው አማካኝነት በድጋሚ አቤቱታውን ያሰማ ሲሆን ፍርድ ቤቱ በትናንትናው ዕለት በዋለው ችሎት አክስዮን ማህበሩ ለባለመብቱ አብዱልሰመድ ክፍያውን እንዲፈፅም ለሁለተኛ ጊዜ ትዕዛዝ አስተላልፏል።