የወቅቱ የሊጉ ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጣይ ዓመት በሚኖረው ተሳትፎ ዙርያ የክለቡ ቦርድ በትናትነው ዕለት ስብሰባ ተቀምጦ የተለያዩ አቅጣጫዎች አስቀምጧል።
ከአምስት ዓመታት በኋላ ለአስራ አምስተኛ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ያነሳው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጣይ በአፍሪካ መድረክ እና በሀገር ውስጥ ውድድር ለሚጠብቀው ፍልሚያ ዘንድሮ ያሳየውን ጥንካሬ ለማስቀጠል በሚቻልበት ዙርያ በትናትናው ዕለት የክለቡ የበላይ አካላት ከአሰልጣኝ አባላቶች ጋር በመሆን ሰፊ ውይይት በማድረግ የተለያዩ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።
በዋናነት ክለቡን ያለፉትን ስምንት ወራት በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ሲመሩ የቆዩት እና የ2014 ኮከብ አሰልጣኝነት ክብር የተቀዳጁት አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በቋሚነት በሚቀጥሉበት ጉዳይ ዙርያ ውይይት ማድረጋቸው ሲሰማ ምን አልባትም በቀጣይ ቀናት አንዳንድ ጉዳዮች ሲጠናቀቁ ዘሪሁን ሸንገታ ዋና አሰልጣኝ ሆነው መሾማቸው በይፋ ይገለፃል ተብሎ ይጠበቃል።
በተያያዘም አሰልጣኝ ዘሪሁን በ2015 በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግም ሆነ ዳግም በሀገር ውስጥ ውድድር ጠንካራ ሆኖ ለመቅረብ ተጨማሪ የሚመጡ ተጫዋቾች ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን ከነገ ጀምሮ ወደ ክለቡ አዳዲስ ተጫዋቾች ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል።