ሀገር በቀሉ የስፖርት ትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ በዩጋንዳ ፕሪምየር ሊግ ለሚሳተፈው ክለብ ትጥቅ ለማቅረብ ዛሬ ስምምነት ፈፅሟል።
ከሰሞኑን ትላልቅ ስምምነቶችን ይፋ እያደረገ የሚገኘው ሀገር በቀሉ የስፖርት ትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ ዛሬ አመሻሽ ቦሌ አካባቢ በሚገኘው ቢሮው በዩጋንዳ ከፍተኛ የሊግ እርከን እየተወዳደረ ከሚገኘው ሞደርን እግር ኳስ ክለብ ጋር የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት ማድረጉን የብዙሃን መገናኛ አባላት በተገኙበት ይፋ አድርጓል። በስፍራው ጎፈሬን ወክለው መስራች እና ሥራ አስኪያጁ አቶ ሳሙኤል መኮንን ሲገኙ በዩጋንዳው ክለብ በኩል ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ኤድሪን ኦቼንግ ታድመዋል። ሁለቱም አካላት ስምምነታቸውን በሚዲያ ፊት በፊርማቸው ካፀኑ በኋላ የተለያዩ ገለፃዎች መደረግ ጀምረዋል። በቅድሚያም አቶ ሳሙኤል መድረኩን ተቀብለው ተከታዩን ሀሳብ አጋርተዋል።
“ዛሬ ስምምነት የፈፀምነው በዩጋንዳ ፕሪምየር ሊግ እየተጫወተ ዓምና 8ኛ ደረጃን ይዞ ካጠናቀቀ ክለብ ጋር ነው። ክለቡ አሁን ባገኘው ስፖንሰር አማካኝነት ስሙን ከጋዳፊ ወደ ሞደርን ቀይሯል። አሁን ከእኛ ጋር የተፈራረሙት የሦስት ዓመት ውል ነው። ክለቡ ከእኛ ከ10 ሺ በላይ የደጋፊዎች ማሊያ ይገዛናል ፤ እኛ ደግሞ የመለያ ስፖንሰራቸው እንሆናለን።
“ይህ ስምምነት ከሀገር ውጪ የተደረገ ሁለተኛው ስምምነት ነው። ስምምነቱ ብዙ ነገር ይከፍትልናል ብለን እናስባለን። ይሄንን አይተው ብዙ ክለቦች አብረውን እንደሚሰሩ እናስባለን። አሁንም እያነጋገርናቸው ያለናቸው ክለቦች አሉ። ስለዚህ ይህ ስምምነት ከሀገር ውጪ ያለውን ገበያ በጥሩ ሁኔታ ይከፍትልናል ብለን እናስባለን።”
አቶ ሳሙኤል በንግግራቸው መጨረሻ በጥራት፣ በገንዘብ እና በምርት ፍጥነት ከሌሎች የስፖርት ትጥቅ አቅራቢ ድርጅቶች ጋር እየተገዳደሩ እንደሆነ ጠቁመው በምስራቅ አፍሪካ አልፎም በአፍሪካ ተመራጭ ለመሆን እየሰሩ እንደሆኑ ተናግረዋል።
የሞደርን ክለብ ፕሬዝዳንት የሆኑት ኤድሪን ኦቼንግ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው ስለስምምነቱ ተጨማሪ ሀሳብ ማጋራት ይዘዋል። “እኔ በፕሬዝዳንትነት የምመራው ክለብ ስሙ ጋዳፊ ይባል ነበር። አሁን ግን በስፖንሰር አማካኝነት የስያሜ መብቱ ወደ ሞደርን ተቀይሯል። ወደ ስምምነቱ ሳመራ ጎፈሬ ነው ከእኛ ጋር ለመስራት ቀድሞ ፍላጎት ያሳየው። እኛም በትክክል ምን እና እንዴት እንደሚሰሩ ለማየት ወደ መቀመጫ ከተማቸው አዲስ አበባ መጥተናል። እዚህ ከመጣን በኋላ ጎፈሬ በሚሰራው ነገር በጣም ነው የተደመምነው። ጥራቱ የሚገርም ነው። የሚያመርቱበት ፍጥነትም ከፍተኛ ነው። ይህንን ታሳቢ በማድረግ ከጎፈሬ ጋር አብሮ ለመስራት ስምምነት ለማድረግ ወስነናል። በዚህም ዛሬ ጎፈሬን ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት የትጥቅ አቅራቢ አጋራችን አድርገን ተፈራርመናል።” ብለዋል። ፕሬዝዳንቱ ጨምረው ከፑማ፣ አዲዳስ እና ጎፈፌ የቀረበላቸውን ምክረ-ሀሳብ (ፕሮፖዛል) ከተመለከቱ በኋላ ኢትዮጵያዊውን ተቋም እንደመረጡ አመላክተዋል።
በስምምነቱ መሰረት ጎፈሬ ለክለቡ በነፃ የሜዳ፣ የሜዳ ውጪ እና የተለየ ሦስተኛ መለያን የሚያቀርብ ሲሆን ክለቡም ከጎፈሬ በዓመት 10 ሺ የደጋፊዎች ማሊያን እንደሚገዛ ተጠቅሷል። በተጨማሪም የጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አቅራቢ ድርጅት እህት ኩባንያ በሆነው ኢቨንይ ኦርጋናይዘር የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ትርዒቶች ተዘጋጅተው በጋራ ተጠቃሚ የሚኮንበት መንገድ እንዳለም ተጠቁሟል።
ከበርካታ የሀገር ውስጥ ክለቦች ጋር የሚሰራው ጎፈሬ ከዚህ ቀደም ከደቡብ ሱዳኑ ማላኪያ ክለብ ጋር ስምምነት ፈፅሞ እንደነበር ይታወሳል።