የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የሊጉ መሪዎች ድል ሲቀናቸው አቃቂ ቃሊቲ መውረዱን አረጋግጧል

21ኛ ሳምንቱ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በአዳማ ሲቀጥል መሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም ተከታዮቹ ኤሌክትሪክ እና ሀዋሳ ከተማን ጨምሮ ባህር ዳር ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ድል ቀንቷቸዋል።

3፡00 ሰዓት ላይ የተደረጉት ጨዋታዎች በሀዋሳ እና ባህር ዳር ድል አድራጊነት ተጠናቀዋል

በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ላይ የዋንጫ ተፎካካሪ ከሆኑ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ሀዋሳ ከተማ አዲስ አበባ ከተማን ገጥሞ እጅግ ተፈትኖም ቢሆን በመጨረሻም ድል አድርጓል፡፡ በአንድ ሁለት ቅብብል እና በተሻጋሪ ኳሶች የመዲናይቱ ክለብ ረዘም ያለውን ደቂቃ ተሽሎ መታየት ቢችልም ከዕረፍት በኋላ ሀዋሳዎች ከተጠባባቂ ወንበር ቀይረው ባስገቧቸው ተጫዋቾች ታግዘው አሸንፈው ወጥተዋል፡፡ 55ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ ወደ ሜዳ የገባችው አጥቂዋ ረድኤት አስረሳኸኝ ከማዕዘን ምት ስታሻማ በተከላካዮች የተጨራረፈን ኳስ በሚገርም ቅልበሳ ኪፊያ አብዱራህማን ግሩም ጎል በማስቆጠር ሀዋሳ ከተማ 1-0 አሸናፊ መሆን እንዲችል አድርጋለች፡፡

በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተመሳሳይ ሰዓት ወጣ ገባ አቋምን እያሳየ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ አቃቂ ቃሊቲን 2-1 ሲረታ አቃቂ ወደ ታችኛው የሊግ ዕርከን መውረዱን አረጋግጧል፡፡ ሳባ ኃይለሚካኤል እና ቤተልሔም ግዛቸው የግዮን ንግስቹን የድል ግቦች ሲያስቆጥሩ ዓይናለም መኮንን አቃቂን ከሽንፈት ያልታደገች ግብ ከመረብ አሳርፋለች፡፡

አርባምንጭ ከተማ እና ጌዲኦ ዲላ ነጥብ ሲጋሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ ላይ ጣፋጭ ነጥብን አግኝቷል

በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ ሁለቱ የደቡብ ክልል ክለቦች አርባምንጭ ከተማ እና ጌዲኦ ዲላ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል፡፡ ሙሉውን ክፍለ ጊዜ አርባምንጭ ከተማዎች ብልጫ ወስደው በተደጋጋሚ ሙከራ ማድረግ የቻሉ ቢሆንም ግብ ማግኘት ሳይችሉ በመቅረታቸው ጨዋታው 0-0 ተቋጭቷል፡፡

በሌላኛው ሜዳ ላይ በተከታታይ ድል እያስመዘገበ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ ከተማን 2-1 አሸንፎ ወጥቷል፡፡ ልማደኛዋ እየሩስ ወንድሙ እና አማካይዋ ቤተልሄም መንተሎ የዕንስት ፈረሰኞቹን የድል ግቦች ሲያስገኙ የአዳማን ብቸኛ ጎል አምበሏ ናርዶስ ጌትነት አስቆጥራለች፡፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሁንም በድል ግስጋሴው ሲቀጥል ኢትዮ ኤሌክትሪክ በተጠባቂው ጨዋታ ከመከላከያ ላይ ነጥብ ወስዷል

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለ መሸነፍ ጉዞውን ያስቀጠለበትን ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ቦሌ ክፍለ ከተማን የገጠመው ክለቡ 2-0 በሆነ ውጤት አሸንፎ ወጥቷል፡፡ የቦሌዋ አማካይ ሂሩት ብርሀኑ በራሷ ላይ መዲና ዐወል ደግሞ ከዕረፍት በኋላ የድል ግቦችን አስቆጥረው የባንክን ያለ መሸነፍ ጉዞ አስቀጥለዋል፡፡

እጅግ ጠንካራ ፉክክርን ያስመለከተን የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና መከላከያ ጨዋታ አጨራረሳቸውን ባሳመሩት የአሰልጣኝ መሠረት ማኔ ተጫዋቾች የበላይነት ተደምድሟል፡፡ እልህ አስጨራሽ የሜዳ ላይ ፉክክር ባስተዋልንበት እና በርካታ ደጋፊዎች በታደሙበት መርሐ-ግብር ሴናፍ ዋቁማ ከዕረፍት በፊት ከግራ አቅጣጫ ያገኘችውን አጋጣሚ ወደ ጎልነት ለውጣ የጦሩን ዕንስቶች ቀዳሚ አድርጋ ወደ መልበሻ ወጥተዋል፡፡ 

ከዕረፍት መልስ በጨዋታው የኢትዮ ኤሌክትሪክ የበላይነት አይሎ በመጨረሻም ባለ ድል አድርጓቸው ተጠናቋል፡፡ የሰላማዊት ጎሳዬ ሁለት እጅግ አስገራሚ ጎሎች አስቆጥራ ኤሌክትሪክ 2-1 ድል አድርጎ መውጣት እንዲችል ሆኗል፡፡