በዝውውር ገበያው ንቁ ተሳታፊ የሆኑት ኢትዮጵያ ቡናዎች ሁለት ወጣት የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾችን አስፈርመዋል፡፡
ለቀጣዩ የውድድር ዓመት ጠንካራ ተፎካካሪ ቡድን ለመገንበት በዝውውሩ ጥሩ ተሳትፎን እያደረጉ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከኃይለሚካኤል አደፍርስ ፣ አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ እና መስፍን ታፈሰ በኋላ አራተኛ እና አምስተኛ ፈራሚ በማድረግ ብሩክ በየነ እና ጫኣን ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል፡፡
ከሀዋሳ ቄራ ሜዳ የተገኘው እና በአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ አማካኝነት 2009 በወልቂጤ ከተማ በመጫወት የክለብ ህይወቱን የጀመረው ወጣቱ አጥቂ ብሩክ በየነ ከ2011 ጀምሮ ወደ ትውልድ ከተማው ሀዋሳ በማምራት ያለፉትን አራት አመታት ለክለቡ በወጥነት ግልጋሎት በመስጠት ቆይቶ በእግር ኳስ ዘመኑ ሦስተኛ ክለቡ በማድረግ ኢትዮጵያ ቡናን በዛሬው ዕለት መቀላቀል ችሏል፡፡
በኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጎልቶ ከወጣ በኋላ በሻሸመኔ ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ የተጫወተው ጫላ ተሺታ ወደ ወልቂጤ ከተማ ዘንድሮ ከተመለሰ በኋላ ጥሩ የውድድር ዘመን ያሳለፈ ሲሆን የኢትዮጵያ ቡናን መስመር ማጥቃት አማራጭ ይሰጠዋል ተብሎ ይጠበቃል።