ፈረሰኞቹ የመስመር አጥቂውን አስፈርመዋል

የወቅቱ የሊጉ ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈጣኑን የመስመር አጥቂ የግሉ አድርጓል።

በአህጉራዊ መድረክም ሆነ በቀጣይ ዓመት ለሚኖራቸው ውድድሮች ራሳቸውን ለማጠናከር በትናትናው ዕለት የግራ መስመር ተከላካዩ ረመዳን የሱፍን የመጀመርያ ፈራሚያቸው በማድረግ የዝውውር ገብያውን የተቀላቀሉት ፈረሰኞቹ አንድ ተጫዋች ማስፈረማቸውን ገልፀዋል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለተኛ ፈራሚ የሆነው የመስመር አጥቂው ቢንያም በላይ ሲሆን ትናንት ከትውልድ ከተማው ድሬዳዋ በመምጣት ከክለቡ ሰዎች ጋር ድርድር ማድረጉ ሲታወቅ ዛሬም በድጋሚ ባደረጉት ምክክር ቢንያም ለሁለት ዓመት ለፈረሰኞቹ ለመጫወት ከስምምነት መድረሱን ክለቡ አሳውቋል።

በ2009 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለቆ ወደ ጀርመን በማቅናት ለዳይናሞ ደርስደን ለመጫወት የሙከራ ጊዜ በማድረግ ወደ አልባንያ ያመራው ቢንያም ከስከንደርቡ ክለብ ጋር በሁለት ስኬታማ ዓመታት የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ካሳለፈ በኋላ በመቀጠልም በስዊድኖቹ ክለቦች ስሪያንስካ እና ኡመያ ክለቦች ቆይታ አድርጓል፡፡ ወደ ሀገሩ በመመለስም ዓምና የውድድር አጋማሹን በሲዳማ ቡና በማሳለፍ ዘንድሮ በመከላከያ ቆይታ ማድረጉ ይታወቃል። የቢንያም ዝውውር ፈረሰኞቹን ካላቸው ጠንካራ የመስመር አጥቂዎቹ አኳያ ተጨማሪ አቅም እንደሚጨምር ሲታመን በዚህ በማያበቃው የዝውውር እንቅስቃሴያቸው በቀጣይ ቀናት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ጥረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።