ከነገ ጀምሮ በረዳት አሰልጣኙ ያሬድ ገመቹ መሪነት ወደ ዝውውር ለመግባት በዛሬው ዕለት በቦርድ ስብሰባ ውሳኔን ያሳለፈው ሀድያ ሆሳዕና ከዋና አሰልጣኙ ጋር ለመለያየት መቃረቡን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በቀጣዩ ዓመት የሦስተኛ ዓመት ተሳትፎውን በማድረግ በውድድሩ ላይ የሚዘልቀው ሀድያ ሆሳዕና በዛሬው ዕለት የቦርድ ስብሰባን አከናውኗል፡፡ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አባተ ተስፋዬ ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት ክለቡ የአንድ ዓመት ቀሪ ውል ከነበራቸው ሀብታሙ ታደሰ ፣ ተስፋዬ አለባቸው ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስ ፣ ባዬ ገዛኸኝ ፣ ሄኖክ አርፊጮ ፣ ሳምሶን ጥላሁን ፣ ኤልያስ አታሮ ፣ መላኩ ወልዴ ፣ አበባየው ዮሃንስ እና አስቻለው ግርማ ጋር የነበራቸውን ውል ስለማቋረጣቸው ነግረውናል።
ቀሪ ውል ያለባቸው ፀጋዬ ብርሀኑ ፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ፣ ብርሀኑ በቀለ እና ፍሬዘር ካሳ እንዲሁም ሌሎች ወጣት ተጫዋቾች በኮንትራታቸው እንደሚቀጥሉ ጨምረው ከገለፁልን በኋላ የክለቡ ቦርድ ዛሬ አመሻሽ ባደረገው ስብሰባ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የአንድ ዓመት ውል ቢኖራቸውም ከክለቡ ጋር ለመለያየት አሰልጣኙ በላኩት የልቀቁኝ ደብዳቤ ስለ መግለፃቸውም ጭምር አስረድተውናል፡፡
እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ ከሆነ የአሰልጣኙን የመልቀቂያ ደብዳቤ በቀጣዮቹ ቀናት ቦርዱ የሚመለከተው ሲሆን ነገርግን የአሠልጣኙ ጉዳይ እስከሚለይ ድረስ ግን ከነገ ጀምሮ ተጫዋቾችን የማስፈረም ሀላፊነት ለረዳት አሰልጣኙ ያሬድ ገመቹ ተሰጥቷል።