ጦሩ የተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾቹን ውል አድሷል

ከደቂቃዎች በፊት የወሳኝ ተከላካዮቹን ውል ያራዘመው መከላከያ የሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾቹን ውልም ማራዘሙ ታውቋል።

በቅርቡ ዋና አሠልጣኙን ይፋ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቀው መከላከያ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ መቀላቀል የጀመረ ሲሆን ጎን ለጎንም የነባር ተጫዋቾቹን ውል በማደስ ላይ ይገኛል። ከደቂቃዎች በፊት የወሳኝ ተከላካዮቹን አሌክስ ተሰማ እና ዳዊት ማሞን ውል ያራዘመው ቡድኑ የተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾችን የመቆያ ጊዜ ማራዘሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በቡድኑ ውሉን ያደሰው ሦስተኛ ተጫዋች የሆነው ሁለገቡ ግሩም ሀጎስ ነው። ከወሎ ኮምቦልቻ ቡድኑን ከተቀላቀለ በኋላ ዓምና ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያድግ አባል የነበረው ግሩም በአማካይ እና በመስመር ተከላካይ ሚና ዘንድሮም ግልጋሎት ሲሰጥ የነበረ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ለሦስት ዓመታት የሚያቆየውን ውል መፈረም ችሏል።

ሌላኛው ተጫዋች ደግሞ የመሐል ተከላካዩ ኢብራሔም ሁሴን ነው። ያለፉትን ሦስት ዓመታት በጥሩ ብቃት ቡድኑን ሲያገለግል የነበረው ኢብራሔም ቡድኑ ዳግም ወደ ሊጉ እንዲያድግ ጉልህ ሚና ከተጫወቱ ተጫዋቾች መካከል አንዱ እንደነበር አይዘነጋም። ውሉ ማለቁን ተከትሎም ለተጨማሪ ሁለት ዓመት ለመቆየት ፊርማውን አኑሯል።

ያጋሩ