22ኛ ሳምንቱ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ንግድ ባንክ ወደ ዋንጫው መቅረቡን ፍንጭ ያሳየውን ውጤት ሲያስመዘግብበት ተከታዮቹን ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀዋሳ ከተማን ጨምሮ መከላከያ ፣ አርባምንጭ እንዲሁም ድሬዳዋ ወሳኝ ድል አግኝተውበታል፡፡
3፡00 ላይ የተደረጉ ጨዋታዎች የሊጉ መሪን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ተከታዩን ኢትዮ ኤሌክትሪክን ባለድል አድርገዋል
በአዳማው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ የሊጉ መሪ ንግድ ባንክ እና አዳማ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ በንግድ ባንክ የበላይነት ተደምድሟል፡፡ ንግድ ባንኮች በተፈተኑበት እና የኋላ ኋላ የአዳማ ከተማን የመከላከል ድክመት በመጠቀም አሸንፈው ወጥተዋል፡፡ 7ኛው ደቂቃ ላይ መዲና ዐወል ወደ ሳጥን ይዛ በመግባት ከመረብ ያሳረፈችው ጎል ባንክን መሪ አድርጎታል፡፡ ከዕረፍት ሲመለስ አዳማዎች በረጃጅም ኳስ ወደ ንግድ ባንክ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም የባንክን ተከላካይ አልፎ ማስቆጠር ግን አቅቷቸው ታይቷል፡፡ በአንፃሩ ተሻለ መነቃቃት የአዳማን የመከላከል አደረጃጀት የበታተኑት የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ተጫዋቾች በሰናይት ቦጋለ ሁለተኛ ጎል ካስቆጠሩ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ የአዳማዋ አጥቂ ሄለን እሸቱ አንድ ግብ አስቆጥራ ጨዋታው ወደ 2-1 ተሸጋግሯል፡፡ የአዳማ ተከላካይ ሣምራዊት ኃይሉ በራሷ ላይ የጨዋታው መጠናቀቂያ ሰዓት ደግሞ ሎዛ አበራ ተጨማሪ ግብ በማስቆጠር ጨዋታው በንግድ ባንክ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሜዳ ላይ መሪው ንግድ ባንክን የሚከተለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጌዲኦ ዲላን አሸንፎ ወጥቷል፡፡ አጥቂዎቹ ምንትዋብ ዮሃንስ እና ትንቢት ሳሙኤል ከዕረፍት በፊት ሁለት ግቦችን ለኤሌክትሪክ ያስቆጠሩ ሲሆን ትንቢት ሳሙኤል በቀድሞው ክለቧ ላይ ነው ማስቆጠር የቻለችው፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አምስት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩ በኤሌክትሪክ በኩል ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እያደረገች ያለችው ዓይናለም አሳምነው ሦስተኛውን አክላ ጨዋታው በኤሌክትሪክ 3-0 መጠናቀቅ ችሏል፡፡
መከላከያ እና አርባምንጭ ከተማ በተመሳሳይ ጎሎች ተጋጣሚዎቻቸውን ረተዋል
አርባምንጭ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማን የገጠመበትን ጨዋታ ተፈትኖም ቢሆን በመጨረሻዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ባሳየው ድንቅ ብቃት ታግዞ አሸንፎ መውጣት ችሏል፡፡ ተመጣጣኝ ፉክክርን ባየንበት እና እንቅስቃሴው መሀል ሜዳ ላይ አመዝኖ በተስተዋለበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 74ኛው ደቂቃ ላይ ትዝታ ኃይለማርያም እና 79ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ መሠረት ወርቅነህ የቦሌ ተከላካዮችን ስህተት ተጠቅማ ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር ጨዋታው በዕንስት አዞዎች የበላይነት ፍፃሜን አግኝቷል፡፡
ጠንካራ ፉክክር የተስተዋለበት እና ባህርዳር ከተማ በርትቶ በተጫወተበት ጨዋታ መከላከያ ድል ተቀናጅቷል፡፡ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሜዳ ላይ በተደረገው በዚህ ጨዋታ መከላከያ ከዕረፍት በፊት በሴናፍ ዋቁማ ሁለት ጎሎች አሸንፎ መውጣት ችሏል፡፡
10፡00 ላይ የተደረጉ ጨዋታዎች ሀዋሳን እና ድሬዳዋን ሦስት ነጥብ አሸምተዋቸዋል
የቅዱስ ጊዮርጊስ የሜዳ ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ሙሉውን የጨዋታ ደቂቃዎች ማየት ባስቻለን ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ፍፁም ተቸግሮም ቢሆን ሙሉ ነጥብን አግኝቷል፡፡ ቀዝቀማ አየርን ተላብሶ በተካሄደው ጨዋታ 16ኛው ደቂቃ ላይ ረድኤት አስረሳኸኝ በሳጥን ውስጥ ያገኘችውን አጋጣሚ በቀጥታ ወደ ጎል ስትመታው በግብ ጠባቂዋ ሲመለስ በቅርብ ርቀት ላይ አነፍንፋ የነበረችው አማካዩዋ ህይወት ረጉ በቀላሉ ወደ ጎልነት ለውጣት ሀዋሳን 1-0 አሸናፊ አድርጋለች፡፡
ድሬዳዋ ከተማ ከሊጉ መውረዱን ያረጋገጠውን አቃቂ ቃሊቲን ገጥሞ 4-1 አሸንፏል፡፡ ለድሬዳዋ ከተማ ቤተልሄም ታምሩ ሁለት ጎሎችን ስታስቆጥር የቀሩትን ሊና መሐመድ እና ሄለን መሰለ ማስቆጠር ችለዋል፡፡ አቃቂን ካለመሸነፍ ያላዳነች ጎል ዓይናለም መኮንን አስገኝታለች፡፡