አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ የውል ስምምነት ፈፅመዋል

አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ለቀጣዩ አንድ ዓመት በኢትዮ ኤሌክትሪክ እንደሚቀጥሉ ዛሬ ክለቡ እና አሰልጣኙ ባደረጉት የውል ስምምነት ተረጋግጧል፡፡

በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ረጅም ታሪክ ካላቸው ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ታችኛው የሊግ ዕርከን ከወረደ ከአራት ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ በተጠናቀቀው የከፍተኛ ሊግ ውድድር የምድብ ሀ ሻምፒዮን በመሆን መመለሱ ይታወሳል፡፡ በቀጣዩ ዓመት ክለቡ በፕሪምየር ሊጉ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችል በዋና አሰልጣኝነት እየመሩ ቡድኑን ያሳደጉት አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ከክለቡ ጋር እንዲቀጥሉ በዛሬው ዕለት በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል በተዘጋጀው የፊርማ ሥነ ስርአት ላይ በይፋ ውል ተፈራርመዋል፡፡

በፊርማ ሥነ ስርአቱ ላይ የክለቡ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጫላ አማን ፣ ስራ አስኪያጁ አቶ አሸናፊ እጅጉ እንዲሁም አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተናን ጨምሮ የክለቡ የበላይ አመራሮች እና እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ጋዜጠኞች ታድመውበታል፡፡ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ እጅጉ ባደረጉት የመግቢያ ንግግር ክንውኑ ከጀመረ በኋላ ክለቡ በሥራ አስኪያጁ በኩል ከአሰልጣኙ ጋር የአንድ ዓመት የውል ተፈራርሟል፡፡

ከፊርማው ሥነ ስርዓት መጠናቀቅ በኋላ የክለቡ የቦርድ አመራር ሰብሳቢ አቶ ጫላ አማን ለአሰልጣኙ የአንድ ዓመት ኮንትራት እንደተሰጣቸው ጠቅሰው በሚያስመዘግቡት ውጤት መሠረትም ውላቸው እንደሚራዘምላቸው ተናግረዋል፡፡ አሰልጣኝ ክፍሌም የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመወጣት ክለቡ በሰጣቸው ዕቅድ መነሻነት በሊጉ ቡድኑን ከአንድ እስከ ስድስተኛ ባለው ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅ እንዲችል ለማድረግ እንደሚጥሩ ገልፀዋል፡፡

ያጋሩ