ጎፈሬ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስምምነት ፈፀሙ

አዲሱ የሊጉ ክለብ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሀገር በቀሉ የትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ ጋር የሦስት ዓመት ስምምነት ፈፅሟል።

ግዙፉ የስፖርት ትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ በሁለቱም ፆታዎች ከፕሪምየር ሊጉ እስከ ታችኛው ዲቪዚዮኖች ከሚገኙ ክለቦች ጋር አብሮ እንደሚሰራ ይታወቃል። በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካም ምህዳሩን እያሰፋ የሚገኘው ተቋሙ ዛሬ አመሻሽ ከአንጋፋው ክለብ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ስምምነት ፈፅሟል።

በሀያት ሪጀንሲ በተከናወነው መርሐ-ግብር ላይ የኢትዮ ኤሌክትሪክ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጫላ አማን እና የጎፈሬ ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን ተገኝተዋል። በቅድሚያም ሁለቱ አካላት የብዙሃን መገናኛ አባላት ፊት ስምምነታቸውን በፊርማ አፅንተው ገለፃ ማድረግ ጀምረዋል።

መድረኩን ቀድመው የተረከቡት አቶ ሳሙኤል ስምምነቱ ለሦስት ዓመት እንደሆነ ገልፀው ተከታዩን ብለዋል። “ዛሬ እዚህ የተገኘነው ታላቁ ክለብ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ጎፈሬ የአጋርነት እና የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት ስለፈፀሙ ነው። ሁለታችንም ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት በጋራ እንሰራለን። ይህ ስምምነት እስከዛሬ ካደረግናቸው ለየት የሚያደርገው በአይነት ከእኛ ምርቶች ውጪ የማይጠቀሙ በመሆኑ እና ክለቡን በደጋፊ መሰረት ለማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎችን ስለሚከወኑበት ነው።” በማለት ጎፈሬ በብቸኝነት የኢትዮ ኤሌክትሪክ እግር ኳስ ክለብ የትጥቅ አቅራቢ እንደሆነ አብስረዋል።

የቦርድ ሰብሳቢው አቶ ጫላ በበኩላቸው “ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ በሁለት ተቋማት የሚተዳደር ክለብ ነው ፤ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል። እነዚህ ተቋማት ለሀገር በቀል ድርጅቶች የሚሰጡትን ማበረታቻ እና ድጋፍ እንዲሁም ለማብቃት የሚሄዱትን ሂደት ልምድ በመውሰድ በስፖርት ክለባችን የሀገር ውስጥ የትጥቅ አምራች ከሆነው ጎፈሬ ጋር አብረን ለመስራት ስምምነት እያደረግን ነው። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ላለፉት 60 ዓመታት የሚጫወትባቸውን ትጥቆች ከውጪ እያስመረተ ነበር የሚጠቀመው። በቅርብ ጊዜ ደግሞ በግዢ ሲጠቀም ቆይቷል። ከዚህ በኋላ ደግሞ የእግር ኳስ ቡድኖቻችን ሙሉ ለሙሉ ከጎፈሬ ጋር በፈፀምነው የትጥቅ አጋርነት ስምምነት መሰረት የምንጠቀም ይሆናል።” ካሉ በኋላ ጎፈሬን የመረጡት የክለቡን አንጋፋነት እና ክብር የሚመጥን ትጥቅ እንደሚያቀርብ ስላመኑ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከእግር ኳሱ ውጪ በርካታ የስፖርት አይነቶችን በስሩ ያቀፈው ኢትዮ ኤሌክሪክ ላሁኑ በወንዶቹ ከ13 ዓመት በታች ጀምሮ እስከ ዋናው ቡድኖቹ ድረስ እንዲሁም ለሴቶቹ ቡድን ብቻ ምርቶቹን እንደሚያቀርብ ተመላክቷል። በቀጣይ ግን የሌሎች የስፖርት ዘርፎች ላይም አብሮ መስራት እንደሚቻል ተጠቁሟል። ጎፈሬ ለቡድኖቹ ከሚያቀርበው ትጥቅ በተጨማሪም የደጋፊዎች መለያን እንደሚያቀርብ ከተገለፀ በኋላ የቡድኑ ትጥቅ ይፋ ሆኖ መርሐ-ግብሩ ተፈፅሟል።