ሀድያ ሆሳዕና በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ዙርያ ውሳኔ አሳልፏል

በቅርቡ የመልቀቂያ ጥያቄ ባቀረቡት አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ዙርያ የክለቡ ሥራ አመራር ቦርድ ከውሳኔ ደርሷል።

ያለፈውን የውድድር ዓመት ሀድያ ሆሳዕናን በዋና አሰልጣኝነት ሲመሩ የቆዩት አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የአንድ ዓመት ቀሪ ኮንትራት እያላቸው በገዛ ፍቃዳቸው ከክለቡ ጋር ለመለያየት የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸው ይታወቃል።

በክለቡ በኩል አሰልጣኙ ያስገቡትን ደብዳቤ ተቀብለው የክለቡ ሥራ አመራር ቦርድ በቅርቡ በጉዳዩ ዙርያ በቀናት ውስጥ ምላሽ እንደሚሰጥ አቶ አባተ ተስፋዬ የክለቡ ሥራ አሰደኪያጅ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀው እንደነበርም ማስነበባችን ይታወሳል።

‘ሁኔታው ከምን ደረሰ ?’ በማለት የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አባተ ተስፋዬ ያናገርን ሲሆን ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል። “ የሥራ አመራሩ ቦርድ ባደረገው ስብሰባ አሰልጣኙ የአንድ ግለሰብን ጥቅም ያስጠበቀ ጥያቄ አቅርበዋል። አንደኛ በመጥፎ ሰዓት የተጫዋቾች ዝውውር በተከፈተበት ጊዜ ሌላኛው አንዳንድ ችግሮችን በምንፈታበት ወቅት መሆኑ አንዳንድ የቦርድ አባላትን ያስቀየመ ቢሆንም አሰልጣኙ በጠቀየቁት መሠረት ውል ለማፍረስ በፌዴሬሽኑ የውል ስምምነት አንቀፅ አራት ንዑስ ቁጥር አራት መሠረት ውሉን ለማቋረጥ ቦርዱ በሙሉ ድምፅ ወስኗል። የእርሱን የወረቀት ጉዳይ ከቋጨን በኋላ ስለ ቀጣይ አሰልጣኝ የምንገልፅ ሲሆን አሁን ለጊዜው በምክትል አሰልጣኙ እንዲመራ ነው የተወሰነው። የቀረውን በሂደት ሥራ አስፈፃሚው የሚወስነው ይሆናል።”