የዋልያዎቹ ተጋጣሚ ታንዛኒያ ገብታለች

በቻን ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የሚገጥመው የደቡብ ሱዳን ልዑክ ትናንት ምሽት የደርሶ መልስ ጨዋታዎቹ የሚደረጉበት ከተማ ገብቷል።

በአልጄሪያ አስተናጋጅነት በሚከናወነው የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ ከደቡብ ሱዳን ጋር እንደተደለደለ ይታወቃል። ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በሀገራቸው የካፍ እና ፊፋ ጨዋታዎችን ማስተናገድ የሚያስችል ስታዲየም ስለሌላቸው የደርሶ መልስ ፍልሚያዎቹ ታንዛኒያ ዳሬ ሰላም ላይ እንደሚካሄዱ መገለፁም ይታወሳል። ለእነዚህ ፍልሚያ ሁለቱም ቡድኖች ሲዘጋጁ የነበረ ሲሆን ከፍተኛ ትኩረት የሰጠ የሚመስለው የደቡብ ሱዳን ልዑካን ቡድንም ቀድሞ ትናንት ምሽት ወደ ስፍራው እንዳቀና ተገልጿል።

በስቴፋኖ ኩዚ የሚመራው ቡድኑ መጀመሪያ ከሁለት ቀናት በፊት ወደ ስፍራው ለማቅናት ማቀዱን የሀገሪቱ የብዙሃን መገናኛዎች ገልፀው የነበረ ቢሆንም ምክንያቱ ባልታወቀ ጉዳይ ሁለት ቀን ገፍቶ ትናንት ምሽት ስፍራው ደርሷል። ቡድኑ ከሀገሩ ሲነሳም በፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት፣ በቦርድ ዳይሬክተሩ እንዲሁም በብሔራዊ ቡድኖች ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አሸኛነት ተደርጎለታል።

በተያያዘ ዜና አዳማ ላይ ዝግጅቱን እያከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በበኩሉ ከነገ በስትያ ረፋድ 4 ሰዓት ላይ ወደ ስፍራው እንደሚያቀና ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሐምሌ 15 እና 24 እንደሚደረግ ቀድሞ ቀጠሮ ቢያዝለትም ሁለተኛው ጨዋታ በሁለቱ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ንግግር ወደ ሐምሌ 21 እንደመጣ ለማወቅ ችለናል።