23ኛ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ንግድ ባንክ የሊጉ ቻምፒዮን እንደሆነ ሲያውጅ በሌሎች ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ድሬዳዋ ከተማ አሸንፈዋል።
3፡00 ላይ የተደረጉ ጨዋታዎች በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ተጠናቀዋል
ረፋድ ላይ ዝናባማ በነበረው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ቦሌ ክፍለ ከተማ ጨዋታ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ ተከናውኖ በኤሌክትሪክ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ሜዳው በዝናብ የተነሳ ውሃ በማዘሉ ኳስን ለማንሸራሸር እጅግ አመቺ ባልነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ልማደኛዋ አጥቂ ንግስት በቀለ ግሩም ጎል አስቆጥራ ቦሌን መሪ አድርጋለች፡፡ ከዕረፍት መልስ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ኤሌክትሪኮች ባደረጉት የተጫዋች ለውጥ ታግዘው ወደ አሸናፊነት መጥተዋል፡፡ ተቀይራ የገባችው ትንቢት ሳሙኤል እና ዓይናለም አሳምነው አከታትለው ባስቆጠሩት ጎል ቡድኑ ከተመሪነት ወደ መሪነት ተሸጋግሯል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲልም በጭማሪ ሰዓት ንቦኝ የን በፍፁም ቅጣት ምት ጎል አክላ 3-1 በኤሌክትሪክ የበላይነት ተጠናቋል፡፡
በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሜዳ ላይ የተደረገው እና ሁለቱን የመዲናይቱ ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዲስ አበባ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ በተከታታይ በየጨዋታው መነቃቃት የሚታይባቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶችን ባለድል አድርጓል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ዓይናለም ዓለማየሁ እና ቤተልሄም መንተሎ ለዕንስት ፈረሰኞቹ የድል ግቦቹን ሲያስቆጥሩ አሪያት ኦዶንግ ብቸኛዋን የአዲስ አበባን ግብ ከመረብ አገናኝታ ጨዋታው 2-1 ተጠናቋል፡፡
ከቀትር በኋላ በተደረጉ ጨዋታዎች ንግድ ባንክ ቻምፒዮን መሆን ሲችል ድሬዳዋም አሸንፏል
8፡00 ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሜዳ ላይ የሊጉን መሪ ንግድ ባንክ እና በደረጃ ሰንጠረዡ ሦስተኛ ላይ የተቀመጠውን ሀዋሳ ከተማን ያገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ በንግድ ባንክ የበላይነት ሲጠናቀቅ ክለቡ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች እየቀሩት የፕሪምየር ሊጉ የዋንጫ ባለቤት መሆን ችሏል፡፡ ልማደኛዋ አጥቂ ሎዛ አበራ ከዕረፍት በፊት ንግድ ባንክ መሪ መሆን የቻለበትን ጎል በማስቆጠር ቡድኗን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡
ከጎሉ በኋላ ሀዋሳዎች የተወሰደባቸውን ብልጫ ለማስመለስ እጅግ ብርቱ ትግል ሲያደርጉ አስተውለናል፡፡ ከመልበሻ ቤት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል 47ኛው ደቂቃ ላይ ሎዛ አበራ ማራኪ ጎል በማስቆጠር የጎል መጠኑን ወደ ሁለት ከፍ ስታደርግ በጨዋታው ሁለተኛ በውድድር ዓመቱ ደግሞ ሰላሳ አራተኛ ጎሏን አስቆጥራለች፡፡ ሀዋሳዎች ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን ጎል በሲሳይ ገብረዋህድ ማግኘት ቢችሉም በመጨረሻዎቹ ሀያ ደቂቃዎች መዲና ዐወል ሁለት ተጨማሪ ጎሎችን አክላ 4-1 ጨዋታው ተጠናቋል፡፡ በውጤቱ መሠረትም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች እየቀሩት የ2014 የሊጉ ቻምፒዮን በመሆን ኢትዮጵያን በመወከል በሴካፋ የቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ የሚሳተፍም ይሆናል።
በሌላ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ መከላከያን ሳይጠበቅ 2-1 ረቷል፡፡ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ የግራ መስመር ተከላካዩዋ ፀሀይ ኢፋሞ እና አማካዩዋ ትሁን አየለ ለድሬዳዋ ጎል ማስቆጠር ስትችል መከላከያን ከሽንፈት ያላዳነች ጎል ሴናፍ ዋቁማ አግብታለች።
በዕለቱ ቀሪ ጨዋታዎች አርባምንጭ ከተማ እና አዳማ ከተማ እንዲሁም ባህርዳር ከተማ እና ጌዲኦ ዲላ ያለ ጎል ተለያይተዋል።