ድሬዳዋ ከተማ ወደ ዝውውር ገበያው ገብቷል

ድሬዳዋ ከተማ በዛሬው ዕለት ሦስት ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የአንድ ተጫዋች ውል አድሷል።

ለቀጣዩ የ2015 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሰልጣኝ ዮርዳኖስ  ዓባይን በዋና አሰልጣኝነት የቀጠረው ድሬዳዋ ከተማ በዛሬው ዕለት የሦስት አዳዲስ ተጫዋችን የግሉ አድርጓል፡፡

ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ በሁለት ዓመት ውል የክለቡ አዲሱ ፈራሚ ሆኗል፡፡ የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም ደግሞ በአዳማ ከተማ ረዘም ያለ ዓመታትን በመጫወት ያሳለፈው ግብ ጠባቂው የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት በግሉ በአዲስ አበባ ከተማ ቆይታው ጥሩ ጊዜን ማሳለፍ የቻለ ሲሆን ለቀጣዩ የውድድር ጊዜ የምስራቁ ክለብ ቀጣይ ማረፊያው ከሰዓታት በፊት ሆኗል፡፡

ዓመቱን በአዲስ አበባ ከተማ ያሳለፈው ኤልያስ አህመድም ሌላው የክለቡ አዲሱ ፈራሚ ሆኗል፡፡ የቀድሞው የባህርዳር ከተማ ፣ ጅማ አባ ጅፋር ፣ ወላይታ ድቻ እና አዳማ አማካይ የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት በመዲናይቱ ክለብ አዲስ አበባ ከተማ ካደረገ በኋላ ቀጣይ መዳረሻው ድሬዳዋ ሆኗል፡፡

ሌላኛው የብርቱካናማዎቹ አዲስ ፈራሚ እያሱ ለገሰ ነው። በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በአዲስ አበባ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ቆይታ የነበረው የመሀል ተከላካዩ ብዙ ተስፋ ቢጣልበትም በአመዛኙ በውዝግቦች የተሞላ ያልተረጋጋ የውድድር ዘመን ያሳለፈ ሲሆን ለከርሞው ግን የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋች መሆኑ ተረጋግጧል።

ድሬዳዋ ከተማዎች በተጨማሪም የሁለገቡን ጋናዊ የመስመር ተጫዋች አብዱለጢፍ መሐመድን ውል ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ማራዘማቸውን እንዲሁ አሰታውቀዋል።