የሴካፋ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ተራዘመ

አትዮጵያ ንግድ ባንክ ተሳታፊ የሚሆንበት የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የምስራቅ አፍሪካ ውድድር የቀን ለውጥ ተደርጎበታል፡፡

ባሳለፍነው ዓመት በአዲስ መልክ ከተጀመሩ ውድድሮች መካከል አንዱ የካፍ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ይጠቀሳል፡፡ የዘንድሮውም ውድድር ለሁለተኛ ጊዜ የሚደረግ ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያ ዳግም በንግድ ባንክ ለሁለተኛ ጊዜ መወከሏ ከሰሞኑ መረጋገጡ ይታወቃል፡፡

በሞሮኮ ለሚደረገው የማጠቃለያ ውድድር የሚበቁ ክለቦችን ለማግኘት በየዞኑ የሚደረጉ ውድድሮች ቀደም ብለው የሚከወኑ ሲሆን የምስራቅ አፍሪካ (ሴካፋ) የሴት ክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ደግሞ በታንዛኒያ አዘጋጅነት እንደሚደረግ ከወራት በፊት ይፋ መሆኑ ይታወሳል፡፡

በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያን የሚወክለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች እየቀሩት የ2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን መሆኑን ከሰሞኑ ማረጋገጥ የቻለ ሲሆን ካፍ ባወጣው ፕሮግራም መሠረትም የሴካፋ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ሀምሌ 21 እንዲጀመር ለሀገራት በተላከ ደብዳቤ ማሳወቁም ይታወሳል፡፡ የ2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ እስከ አሁን አለመጠናቀቁን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ለሴካፋ አመራሮች የይራዘምልን ጥያቄን ያቀረበ ሲሆን በመጨረሻም በቂ የዕረፍት እና የዝግጅት ጊዜ ለክለቡ እንዲኖረው በሚል ሴካፋ ውድድሩን ወደ ነሀሴ 8 ማራዘሙን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች፡፡