አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከታንዛኒያው ጉዞ በፊት መግለጫ ሰጥተዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከደቡብ ሱዳን አቻው ለሚጠብቁት የማጣሪያ ጨዋታዎች ያደረገውን ዝግጅት የተመለከተ ማብራሪያ በዋና አሰልጣኙ ተሰጥቷል።

የ2023 የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) በአልጄሪያ አዘጋጅነት እንደሚከወን ሲጠበቅ የውድድሩ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች በቅርብ ቀናት ይደረጋሉ። ከዚህም መካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ታንዛኒያ ላይ ደቡብ ሱዳንን የሚገጥምባቸው ሁለት ጨዋታዎች ተጠባቂ ናቸው። ለቅድመ ማጣሪያው ዝግጅት ላይ የከረመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነገ ወደ ታንዛኒያ የሚበር ሲሆን ዛሬ ከምሳ በኋላ በፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት የዝግጅት ጊዜውን የተመለከተ መግለጫ ተሰጥቷል።

የዕለቱን መግለጫ በብቸኝነት የሰጡት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የብሔራዊ ቡድኑን የዝግጅት ቆይታ የተመለከተ ማብራሪያ በመስጠት ጀምረዋል። አሰልጣኙ ሊጉ ከተጠናቀቀ በኋላ ለተጨዋቾች ዕረፍት በመስጠት ጥሪ አድርገው ሐምሌ 04 እና 05 ቅድመ ምርመራ በማድረግ ከሐምሌ 06 ጀምሮ በአዳማ ከተማ ዝግጅት እንደጀመሩ በማስታወስ ነበር መግለጫቸውን የጀመሩት። ሊጉ የፈጠረው ድካም እና ወቅቱ የዝውውር በመሆኑ ተጫዋቾች ላይ የሚፈጥረው ጫና በዝግጅት ጊዜው ላይ የአዕምሯዊ እና አካላዊ ድካም መፍጠሩን ያነሱት አሰልጣኝ ውበቱ በማገገሚያ እና ታክቲካል ስራዎች ላይ ያተኮረው መሰናዶ ለአምስት ቀናት በቀን አንዴ ቀሪውን አንድ ቀን ደግሞ ሁለት ጊዜ መደረጉን ተናግረዋል። ውድድሩ በሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ ከመከወኑ አንፃር ሰለተጋጣሚያቸው የደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ቡድን ከሰኔ 28 ጀምሮ ወደ ዝግጅት ከመግባቱ በቀር ተጨማሪ መረጃ እንደሌላቸው ያነሱት አሰልጣኙ በዋልያዎቹ በኩል ግን ከ23 ተጫዋቾች መካከል አማኑኤል ዮሐንስ ፣ ዳዋ ሆቴሳ እና በዛብህ መለዮ ላይ ከነበረው መጠናኛ ጉዳት በቀር ስብስቡ ሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በመቀጠል አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

የሊጉ ውድድር እና የዝውውር ጊዜው የፈጠሩትን ተፅዕኖዎች ለመቀነስ ስለተደረገው ጥረት

“የዝግጅት ጊዜው አጭር ከመሆኑ አንፃር ልጆቹን ከውድድር ወደ ውድድር መክተት አንዱ ፈታኝ ነገር ነው። ሁለተኛ አዕምሯቸው ያተረጋጋ ልጆች አይደሉም ፤ ከፊርማ ጋር ተያይዞ ወደዛም ወደዚህም ብዙ ንግግሮች እና ውጣ ውረዶች ያሉበት ሊግ ላይ ስለሆነ ያለነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ልጆቹን ከዛ እንዳይወጡ አድርጎ እንዳይንቀሳቀሱ አድርጎ የብሔራዊ ቡድኑ ሥራ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ማድረግ በፍፁም ሊሞከር የማይችል ነገር ነው። በአካል ልንይዛቸው እንችላለን ግን በተለያየ መንገድ ለእኛ የሚሰጡትን ትኩረት ሊቀንሱት ይችላሉ። ያ እንዳይሆን በተቻለ መጠን አንዳንዶቹን ከልምምድ ውጪ ባለ ሰዓት ላይ በተለይ አዲስ አበባ ላይ ባለንበት ወቅት ንግግሮቻቸውን እዛው ሆቴል አካባቢ እንዲያደርጉ ሌሎች የተጠናቀቀ ነገር ያላቸውንም ለፊርማ ደርሰው እንዲመጡ በመፍቀድ ሁለቱንም ነገር እያቻቻልን ለመሄድ ነው የሞከርነው። በመጨረሻ የነበሩ የተወሰኑ ዝውውሮችን ግን እዛው አዳማ እኛ ያለንበት ድረስ ከፌዴሬሽኑ የተወከሉ ሰዎች መጥተው ዝውውር እንዲያከናውኑ እና ልጆቹ እዛው ተረጋግተው እንዲቆዩ ለማድረግ ነው የሞከርነው። ”

አዳዲስ ተጫዋቾችን በብዛት ስላለማካተታቸው

“አሁን ካሉት ውጪ ሌሎችንም ለማሳተፍ አማራጭ ሊሆን ይችላል። ግን በምንፈልገው ደረጃ ቡድኑን ከመገንባት አንፃር ክረምት ላይ ሌሎች ልጆችን አናገኝም። እነዚህንም ልጆች በዚህ ውድድር ባናሳልፋቸው እና ተጨማሪ ዕረፍት ሰጥተናቸው ቢሆን መስከረም ላይ ለሚጠብቀን የጊኒ ጨዋታ እንደገና እንደ አዲስ ነው ለቅድመ ዝግጅት የምናመጣቸው። እነዚህን ጨዋታዎች ማግኘት በራሱ ለቡድኑ ተጨማሪ ጥቅም ነው። ከዛ አንፃር የነበረውን ቡድን ማስቀጠል እና የተወሰኑ ተጫዋቾችን መጨመርን ነው እንደ አማራጭ የወሰድነው።”

ስለተጫዋቾች ከውድድር መምጣት ፈተናዎች

“ከውድድር ወደ ውድድር መሄድ አድካሚ ነው። የእኛ ልጆች ደግሞ እንዲህ ዓይነት ጫና የመቋቋም ነገራቸው አስቸጋሪ ነው። ይሄ አዲስ ምዕራፍ ነው። ቻን እንደገና አዲስ ውድድር ነው። ለሀገራችንም ለተጫዋቾቹም ለእግርኳስ ቤተሰቡም ሌላ ዕድል ነው። አፍሪካ ዋንጫ ላይ የጀመርነው መንገድ አለ። አሁን ደግሞ በዚህ የቻን ውድድር ቢያንስ እስከ አልጄሪያ ማጣሪያውን ለማለፍ እንዲሰሩ እና በዛ ሀሳብ ውስጥ እንዲጠመዱ ለማድረግ እያነሳሳን ነው ያለነው። ከባድ ነው ፤ ምክንያቱም ሙሉ ሲዝን ተጫውቶ ሳያገግሙ ወደ ሌላ ጨዋታ መሄድ። ያንንም ግን በተቻለ መጠን ለመጠበቅ እየሞከርን ነው። ”

ስለደቡብ ሱዳን በቂ መረጃ ስላለማግኘታቸው

“ተጋጣሚን አለማወቅ ይጎዳናል። ያ ማለት ቢያንስ ዝግጅታችንን በተወሰነ መልኩ ጎዶሎ ሊያደርገው ይችላል። የሚመስለውን ነገር መገመት ግን ይቻላል። ደቡብ ሱዳን በአፍሪካ ዋንጫ ደረጃ ያለችበትን ነገር እና ሌሎች ጨዋታዎቿንም አይተናል። ከሞሪታንያ እና ሌሎች ጨዋታዎች ለማየት ሞክረናል። ግን ያ ቡድን አይደለም ለቻን ማጣሪያ የሚመጣው። ግማሾቹ አዲስ እንደሚሆኑ እንገምታለን ፤ ቢያንስ ግን ምን ዓይነት ጨዋታ ሊጫወቱ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል። ይበልጥ ትኩረት ያደረግነው በራሳችን ቡድን ላይ እና የጀመርነውን ነገር በማጠናከር ላይ ነው።”

ስለ ዋና አሰልጣኝነት ኮንትራታቸው

“ኮንትራቴ የሚያበቃው መስከረም ላይ ነው። እንዳለመታደል ሆኖ በእኛ ሀገር እንዲህ ዓይነት ነገር አልተለመደም። ኮንትራት የሚጠናቀቅበት ቀኗን ነው የምንጠብቀው። ከአሰልጣኞች ጋር ተያይዞ እንዲህ ዓይነት ነገሮች መጀመር ያለባቸው ቢያንስ ሦስት ወር ከበዛ ስድስት ወር ላይ ነው። አሰልጣኙም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም በዛ ጉዳይ ላይ አንድ ነገር ላይ መድረስ ይኖርባቸዋል። ሌላው ቀርቶ ለሁለታችንም ክፍት ስለሆነ ሌሎች የእንቅጠርህ ጥያቄዎች ቢኖሩ እኔም ቡድኑን በመሀል ጥዬው ልሄድ የምችልበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል። ቀድሞ አለመነጋገር የሚያስከትለው አደጋ እንደሱ ዓይነት ነገር ነው። ከፌዴሬሽኑ ጋር ንግግር ጀምረናል። በሁለታችንም በኩል አዎንታዊ ነገር አለ። ዝርዝር ነገሮች ላይ ግን ማውራት ይጠበቃል። ከዛ በኋላ ያለውን ነገር ግን ሂደቱ ነው የሚወስነው። በእኔ በኩል የጀመርኩትን ነገር የመጨረስ ፍላጎት አለ ፣ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑም በኩል የተጀመረው ነገር እንዲቀጥል ፍላጎት አለ። ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ተነጋግረን መግባባት ይጠበቃል። ይሄ በቅርብ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።”

የኮንትራት አለመራዘም ስለሚፈጥረው ተፅዕኖ

“የሚፈጥረው አዕምሯዊ ነገር ግን አለ። ባቀጣይ ድንገት ተነስተህ አንድ ኮንትራት አግኝቻለሁ ብለህ ከቦታው ላይ ብትነሳ የራስህ ገፅታ ላይ የሚፈጥረው ጥላ አለ። ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ላይ የሚፈጠረው አለመረጋጋት እና ቡድኑ ላይ የሚፈጥረውም ክፍተት ይኖራል። ያንን ብለህ ደግሞ ዝም ብለህ ደጅ የምትጠና ከሆነ ደግሞ ሌሎች በግል የሚያመልጡ ብዙ ነገሮች አሉ። ያ እንዳትረጋጋ ያደርግሀል። በቅርቡ ግን ዝርዝር ነገሮችን ለማውራት መግባባት ላይ ደርሰናል።”

በመጨረሻም አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ እየተሳተፉ እና ድሎችን እያስመዘገቡ ያሉት አትሌቶቻችን እና ልዑካን ቡድኑን በማመስገን ድሉ የፈጠረባቸውን ስሜት ገልፀው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት በማስተላለፍ መግለጫቸውን ቋጭተዋል።