ዊልያም ሰለሞንን የማስፈረሙ ሂደት ሁለት ክለቦችን አወዛግቧል

ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በስምምነት ከተለያየ በኋላ ወደ ሲዳማ ቡና እንዳቀና የተነገረለት የዊልያም ሰለሞን ዝውውር ውዝግብ አስነስቷል።

ከቀናት በፊት ዊልያም ሰለሞን ከሲዳማ ቡና ጋር ለሁለት ዓመት የሚያቆየውን ስምምነት መፈፀሙን ክለቡ በፎቶ ማስረጃ ይፋ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል። ሆኖም ተጫዋቹ ከሲዳማ ቡና ጋር ያደረገውን ስምምነት በመተው በትናትናው ዕለት ለአዳማ ከተማ ለመጫወት ፊርማውን አኑሯል።

በዚህ ሂደት ደስተኛ ያልሆኑት ሲዳማ ቡናዎች ‘የዊልያም የተጫዋች ተገቢነት ለእኛ ነው በክልል ፌዴሬሽን የተስማማበትን ውል አፀድቀናል ፤ ለዚህም የተፈራረመበት ህጋዊ ሰነድ በእጃችን ይገኛል’ በማለት ለፌዴሬሽኑ አቤቱታቸውን አቅርበዋል። አዳማዎች በበኩላቸው ዊልያም ለሲዳማ ቡና ሲፈርም መልቀቂያ እንዳልሰጠ ፣ የተጫዋች መታወቂያ (ቲሴራ) ላይ እንዳልፈረመ እና ቅድመ ክፍያ እንዳልተቀበለ በመግለፅ ለአዳማ ከተማ የተሟል ሰነድ በማቅረብ ፊርማውን ማኖሩን ማረጋገጫ በመያዝ ‘ተጫዋቹ ለእኛ ይገባል ፤ ፌዴሬሽኑ ዝውውሩን ያፅድቅልን’ በማለት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። በሁለቱ ክለቦች መካከል የዊልያም የይገባኛል ጥያቄን ለመመለስ ጉዳዩን የያዘው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በቅርቡ ሁኔታውን መርምሮ ምላሽ እንደሚሰጥ ሰምተናል።

ዊልያም ከዚህ ቀደም ወደ ኢትዮጵያ ቡና ለማምራት በሚያደርገው ዝውውር ወቅት ከመከላከያ ጋር ለወራት የቆየ ክርክር መፈጠሩ ይታወሳል።

ያጋሩ