የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የዞኑ ማጣሪያ የምድብ ድልድል ይፋ ሆኗል

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚሳተፍበት የቻምፒየንስ ሊግ የምስራቅ አፍሪካ ማጣሪያ የምድብ ድልድል ከደቂቃዎች በፊት ይፋ ሆኗል።

ከዓምና አንስቶ መደረግ የጀመረው የሴቶች የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ዘንድሮም በሞሮኮ ራባት የሚካሄድ ሲሆን በየቀጠናው የማጣሪያ ጨዋታዎችም ከቀናት በኋላ መደረግ ይጀምራሉ። ኢትዮጵያ በምትገኝበት ቀጠና የሚገኙ የስምንት ሀገራት ክለቦች ደግሞ ከነሐሴ 8 ጀምሮ ታንዛኒያ ላይ ፍልሚያቸውን የሚያደርጉ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የምድብ ድልድሉ ይፋ ሆኗል።

የምድብ አንድ አባት የሆነው የሀገራችን ተወካይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዋሪየርስ ኩዊንስ (ዛንዚባር)፣ ፎፊላ ፒኤፍ (ቡሩንዲ) እንዲሁም ኤ ኤስ ኪጋሊ (ሩዋንዳ) ተደልድሏል።

በወጣው መርሐ-ግብር መሠረት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከዛንዚባሩ ዋሪየርስ ኩዊን ጋር የሚያደርግ ሲሆን ሁለተኛውን ደግሞ ከቡሩንዲው ፎፊላ ፒኤፍ ጋር አከናውኖ የመጨረሻ የምድን ጨዋታውን ከኤሴስ ኪጋሊ ጋር የሚያከናውን ይሆናል።

በሌላኛው ምድብ ሲምባ ኩዊንስ (ታንዛኒያ)፣ ጂአር ኤፍ ሲ (ጂቡቲ)፣ ሺ ኮርፖሬት (ዩጋንዳ) እና ዬ ጆይንት ስታርስ (ደቡን ሲዳን) ተደልድለዋል።

የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ነሐሴ 8 እና 9 ሲደረጉ ሁለተኛ ጨዋታዎች በ11 እና 12 ሦስተኛ ደግሞ በ14 እና 14 እንደሚደረጉ ይፋ ሆኗል።