ግብፅ አዲስ አሠልጣኝ ሾማለች

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በኢትዮጵያ ምድብ የምትገኘው ግብፅ ከደቂቃዎች በፊት ፖርቱጋላዊውን አሠልጣኝ በይፋ ሾማለች።

በ2023 በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ አራት ከግብፅ፣ ጊኒ እና ማላዊ ጋር ተደልድሎ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል። በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የተጫወተችው ግብፅ ከከፍተኛ ብልጫ ጋር ሁለት ለምንም ከተረታች በኋላ ወደ ደቡብ ኮሪያ አምርታ ባደረገችው የአቋም መለኪያ ጨዋታ ስትረታ የ54 ዓመቱን አሠልጣኝ ኢሀብ ጋላል ከሦስት ጨዋታዎች ቆይታ በኋላ ከመንበሩ አንስታ ነበር።

ግብፃዊው አሠልጣኝ ከቦታቸው ከተነሱ በኋላ ከፍ ያለ ስም ያለው አሠልጣኝ ከሀገር ውጪ ለማምጣት ሲንቀሳቀስ የነበረው የሀገሪቱ የእግር ኳስ ማኅበርም ከደቂቃዎች በፊት በሰጠው ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ፖርቱጋላዊውን ሩይ ቪቶሪያ መቅጠሩን ይፋ አድርጓል።

የዩ ኤፋ ፕሮ ላይሰንስ ባለቤት እንደሆኑ የሚነገረው የ52 ዓመቱ አሠልጣኝ ከቀናት በፊት ቡድኑን እንደሚይዙ ተገልፆ የነበረ ቢሆንም በይፋ ለብዙሃን መገናኛዎች የበሰረው ከደቂቃዎች በፊት ነበር። የቀድሞ የስፓርታክ ሞስኮ፣ ቪቶሪያ ጉማሬሽ እና ቤኔፊካ አሠልጣኝ የነበሩት ሩይ ቪቶሪያ ከቡድኑ ጋር ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት ለመቆየት ፊርማቸውን እንዳኖሩም ተገልጿል።