ነብሮቹ የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር ሲፈፅሙ የአንድ ተጫዋች ውል አድሰዋል፡፡
ከሰሞኑ አሰልጣኙን ይፋ እንደሚያደርግ የሚጠበቀው ሀድያ ሆሳዕና በዛሬው ዕለት የዝውውር መስኮቱን ተቀላቅሏል፡፡ በዚህ መሠረት ቡድኑ ሁለት አዳዲስ ፈራሚዎች ሲያገኝ የመሀል ተከላካዩን ውልም አድሷል፡፡
ተከላካዩ ዳግም ንጉሴ አዲሱ የክለቡ ፈራሚ ሆኗል፡፡ የቀድሞው የወላይታ ድቻ እና አዲስ አበባ ከተማ ተጫዋች የሆነው ዳግም ሲዳማ ቡናን ከለቀቀ በኋላ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመናት በወልቂጤ ከተማ ሲጫወት አሳልፎ ቀጣይ ማረፊያውን በአንድ ዓመት ውል በሀድያ ሆሳዕና አድርጓል፡፡
በመስመር አጥቂነት እና በአማካይ ስፍራ ተጫዋቾችነት የሚታወቀው ቤዛ መድኅን በሀድያ ሌሙ እንዲሁም በተጠናቀቀው ዓመት በገላን ከተማ ፣ በሀምበሪቾ ዱራሜ እና በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ በወልቂጤ ከተማ በድምሩ በሦስት ክለቦች ውስጥ በመጫወት ያሳለፈ ሲሆን ሁለተኛው የክለቡ አዲሱ ፈራሚ ሆኖ በሁለት ዓመት ውል ነብሮቹን ተቀላቅሏል፡፡
ተከላካዩ ግርማ በቀለ ለተጨማሪ ዓመት በክለቡ የሚያቆየውን ኮንትራት አድሷል፡፡ የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ፣ ንግድ ባንክ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሲዳማ ቡና ተከላካይ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አጋማሽ ላይ በተቀላቀለው ክለብ ተጨማሪ ሁለት የውድድር ዘመናትን ለማሳለፍ ውሉን ዛሬ አራዝሟል፡፡