የሴቶች ፕሪምየር ሊግ |አዲስ አበባ ንግድ ባንክን ሲረታ ኤሌክትሪክ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ መፈፀሙን አረጋግጧል

ሊጠናቀቅ የሁለት ሳምንት ጨዋታዎች የቀሩት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉበት የሊጉ ቻምፒዮን የሆነው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ሽንፈት ሲገጥመው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዓመቱን ሁለተኛ ሆኖ መፈፀሙን አረጋግጧል፡፡ ድሬዳዋ ፣ ቦሌ እና መከላከያም ተጋጣሚዎቻቸውን ረተዋል፡፡

ሀዋሳ በጭማሪ ደቂቃ ጎል ከአርባምንጭ ጋር ነጥብ ሲጋራ ድሬዳዋ ከተማ አምስት ጎሎችን አስቆጥሮ ሙሉ ነጥብ አሳክቷል

3፡00 ላይ ሀዋሳ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ተከናውኗል፡፡ እጅግ የበረታ የሜዳ ላይ ፉክክርን ባየንበት ጨዋታ ምንም እንኳን የዝናቡ ሁኔታ ኳስን ለማንሸራሸር ምቹ መሆን ባይችልም ተጋጤሚዎቹ በቻሉት መጠን ሲያደርጉ የነበረው የሜዳ ላይ ትግል ለተመልካቹ አዝናኝ ነበር፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ወደ ጎል መድረስ የቻሉ ሲሆን ሀዋሳዎች 34ኛው ደቂቃ ላይ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው አጥቂዋ ነፃነት መና ብትመታውም ግብ ጠባቂዋ ምህረት ተሰማ ያዳነቻት አጋጣሚ ልዩነት ለመፍጠር የተቃረበች ብትሆንም ወደ ጎልነት መለወጥ ግን ሳትችል ተሸጋግሯል፡፡

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል የቀድሞው ክለቡን በተቃራኒው እየገጠመ የሚገኘው አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ጥቃት ለመሰንዘር ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት በመስመር አጨዋወት ፈጠን ብለው ለመጫወት የሞከሩት ሀዋሳዎች 64ኛው ደቂቃ ላይ በቱሪስት ለማ የጭንቅላት ጎል መሪ መሆን ችለዋል፡፡ ነገር ግን ጨዋታው ሊገባደድ ሁለት ያህል ደቂቃ ሲቀር አርባምንጮች አቻ መሆን የቻሉበትን ጎል አግኝተዋል፡፡ ከቅጣት ምት ተቀይራ የገባችው መሠረት ወርቅነህ አስገራሚ ጎልን ከመረብ አሳርፋ ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል፡፡

በተመሳሳይ ሰዓት በሌላኛው ሜዳ ላይ ጌዲኦ ዲላ እና ድሬዳዋ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ የምስራቁ ክለብ በጎል ተንበሽብሾ 5-1 በሆነ ውጤት ተጋጣሚውን ረምርሟል፡፡ ከዕረፍት በፊት በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ቤተልሄም ታምሩ ሁለት ጎሎችን አስቆጥራ ቡድኗን ቀዳሚ ማድረግ ስትችል ከመልበሻ ቤት መልስ 68ኛ ደቂቃ ላይ ይታገሱ ተገኝወርቅ ጌዲኦ ዲላን ወደ ጨዋታ የመለሰች ጎል ለቡድኗ ብታስገኝም ታደለች አብርሃም አንድ እና የቀድሞዋ የአርባምንጭ ከተማ አጥቂ ሰርካለም ባሳ በጭማሪ ደቂቃ ሁለት ጎሎችን አክላ ጨዋታው 5-1 በድሬዳዋ የበላይነት ተጠናቋል፡፡

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለተኛ ሆኖ መፈፀሙን ሲያረጋግጥ ቦሌ ክፍለ ከተማም ድል አድርጓል


8፡00 ላይ በአዳማው አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያደረጉት ጨዋታ ጅምሩን አድርጓል፡፡ የመጀመሪያዎቹን ሀያ ደቂቃዎች የአዳማ ከተማ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መታየት በቻለበት ጨዋታ ገና በጊዜ ነበር ጎል ማግኘት የቻሉት። 7ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ አማካዩዋ ቅድስት ዘለቀ ግሩም ጎል ከመረብ አገናኝታ ቡድኗን 1-0 አድርጋለች፡፡ ጎል ካስተናገዱ በኋላ ፍፁም ብልጫን ወስደው ለመንቀሳቀስ የሞከሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች አከታትለው ያስቆጠሯቸው ጎሎች ወደ መሪነት አሸጋግሯቸዋል፡፡ ትንቢት ሳሙኤል በአንድ ሁለት ቅብብል ከዙለይካ ጁሀድ ያገኘችውን ኳስ ወደ አቻነት ስትለውጠው 45ኛ ደቂቃ ላይ ትዕግስት ኃይሌ ለማሻማት በሚመስል መልኩ ያሻገረችው ኳስ ወደ ጎልነት ተለውጦ ውጤቱ ወደ 2-1 ተሸጋግሯል፡፡

ከዕረፍት መልስ የአዳማ ከተማ መዳከም እና የአሰልጣኝ መሠረት ማኔ ተጫዋቾች ብርቱነት አይሎ የተንፀባረቀበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ተከላካዩዋ ዘለቃ አሰፋ እና ወደ ቀድሞው አቋሟ በደንብ መመለስ የቻለችው አይናለም አሳምነው ተጨማሪ ጎሎችን በማስቆጠር ኢትዮ ኤሌክትሪክ 4-1 አሸናፊ በመሆን ውድድሩን በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ላይ ተቀምጦ ማጠናቀቁን ማረጋገጥ ችሏል፡፡

በተመሳሳይ ሰዓት የተደረገው የቦሌ ክፍለ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ በአሰልጣኝ ቻለው ለሜቻው ቡድን የበላይነት ተደምድሟል፡፡ ሜላት አልሙዝ ከዕረፍት በፊት አንድ እና ንግስት በቀለ ከዕረፍት መልስ ሁለት የድል ጎሎችን ለቦሌ ሲያስቆጥሩ ትዕግስት ወርቄ ብቸኛዋን የባህር ዳር ጎል አስቆጥራ ጨዋታው 3-1 ሊያልቅ ችሏል፡፡

የሊጉን ዋንጫ ያነሳው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመጀመሪያ ሽንፈቱን ሲቀምስ መከላከያ የጎል ጥሙን አርክቶ አሸንፏል


ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመጀመሪያ ሽንፈቱን ከሀያ ሁለት ጨዋታዎች በኋላ ቀምሷል፡፡ አዲስ አበባ ከተማን የገጠመው ቡድኑ በዘጠና ደቂቃ ውስጥ ብርቱ ትግል ገጥሞት ተስተውሏል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ ፉክክርን በሁለቱም ክለቦች በኩል በሜዳ ላይ ካደረጉት እንቅስቃሴ መረዳት ብንችልም ከዕረፍት መልስ አብዛኛዎቹን ቋሚ ተሰላፊዎቹን ወደ ተጠባባቂ አውርዶ የነበረው ንግድ ባንክ ወደ ሜዳ ከመለሰ በኋላ ብልጫ ማሳየት ቢችልም የኋላ ኋላ ጨዋታው ተጠናቆ በጭማሪ 90+3 ላይ በረጅሙ ከተሻጋሪ ኳስ አሪያት ኦዶንግ የደረሳትን ኳስ ወደ ጎልነት በመለወጥ አዲስ አበባ ከተማ 1-0 በሆነ ውጤት እንዲያሸንፍ አድርጋለች።

መከላከያ በጎል ተንበሽብሾ አቃቂ ቃሊቲን ረምርሟል፡፡ በአዳማው ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሜዳ ላይ ጨዋታቸውን ሁለቱ ቡድኖች ከውነው ሰባት ጎሎች አስመልክቶ ፍፃሜን አግኝቷል፡፡ ገና በጊዜ ስራ ይርዳው ለመከላከያ ጎል አስቆጥራ ቡድኑ መሪ መሆን ቢችልም ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ማህሌት ኃይሉ አቃቂን አቻ አድርጋለች፡፡ 12ኛው እና 15ኛው ደቂቃ ላይ ሴናፍ ዋቁማ ሁለት ጎሎችን አከታትላ በማስቆጠር የጦሩን ዕንስቶች ወደ 3-1 መሪነት ስታሸጋግር ከደቂቃዎች በኋላም ተጨማሪ ሁለት ጎሎችን ጨምራ ለክለቧ አምስተኛ ለራሷ አራተኛ ግብን ከመረብ አዋህዳለች፡፡ ከዕረፍት መልስ መሳይ ተመስገን ስድስተኛ ጎል ለቡድኗ አስገኝታ ጨዋታው 6-1 በመከላከያ አሸናፊነት ተገባዷል፡፡