ብርቱካናማዎቹ ተጨማሪ ተጫዋች አስፈርመዋል

ድሬዳዋ ከተማዎች አምስተኛ አዲስ ፈራሚያቸውን አግኝተዋል።

ዮርዳኖስ አባይን ዋና አሠልጣኛቸው ካደረጉ በኋላ ፊታቸውን ወደ ተጫዋቾች ዝውውር ያዞሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ከዚህ ቀደም የግብ ዘቡን ዳንኤል ተሾመ ጨምሮ ተከላካዩ እያሱ ለገሠ እንዲሁም አማካዮቹን ኤሊያስ አህመድ እና ዮሴፍ ዮሐንስን ያስፈረሙ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ተጨማሪ ተጫዋች የግላቸው ማድረጋቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ቡድኑን የተቀላቀለው ተጫዋች ጫላ በንቲ ነው። አጥቂው ከኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከተገኘ በኋላ በመከላከያ ተስፋ ቡድን፣ በነቀምት ከተማ እና በሀምበሪቾ ዱራሜ በመጫወት ቆይታ የነበረው ሲሆን ከ2011 ጀምሮ ያለፉትን አራት አመታት ለቡራዩ ከተማ በመጫወት አሳልፎ ነበር። በተጠናቀቀው የዘንድሮ የከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ውድድር ስድስት ግቦችን ያስቆጠረው ይህ ተጫዋች በውሰት ወደ ጅማ አባ ጅፋር አቅንቶ ሲጫወት የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ወደ ምስራቁ የሀገራችን ክፍል በማምራት የሁለት ዓመት ውል አስሯል።

ያጋሩ