ኢትዮጵያ ቡና የአማካይ ስፍራ ተጫዋች አስፈርሟል

ያለፉትን ዓመታት በሀዋሳ ከተማ መለያ የቆየው አማካይ ቀጣይ ማረፊያው ኢትዮጵያ ቡና ሆኗል።

የከርሞው ቡድናቸውን በመገንባት ሂደት ውስጥ ቀደም ብለው ወደ እንቅስቃሴ የገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች አዳዲስ ተጫዋቾችን ማስፈረማቸውን ቀጥለዋል። ከፕሪምየር ሊጉ ባለፈ ወደ ከፍተኛ ሊግ እና የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ጭምር ተጫዋቾችን ሲመለምሉ የሰነበቱት ቡናዎች ዛሬ ደግሞ በሀዋሳ ከተማ ሲጫወት የቆየውን አማካይ በእጃቸው አስገብተዋል።

አዲሱ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች የሆነው አማካይ ሄኖክ ድልቢ ነው። ሄኖክ በሀዋሳ ከተማ የዕድሜ ዕርከን ቡድኖች ውስጥ በማለፍ ለዋናው ቡድን ከ2009 ጀምሮ በመጫወት እንዳሳለፈ ይታወቃል። ተጫዋቹ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ደግሞ በኢትዮጵያ ቡና መለያ እንደምንመለከተው እርግጥ ሆኗል።

ያጋሩ