የኢትዮጵያ የፀረ አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን በመከላከያው የመሀል ተከላካይ ላይ አላስፈላጊ ንጥረ ነገር አግኝቻለሁ በማለት የዕግድ ውሳኔ አስተላልፎበታል፡፡
በተጠናቀቀው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሀዋሳ ከተማ ሲደረግ የኢትዮጵያ የፀረ አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ከአስራ ስድስቱም የሊጉ ተካፋይ ክለቦች የተወሰኑ ተጫዋቾችን በመምረጥ ምርመራ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ የፀረ አበረታች ምርመራ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ የነበረው የመከላከያው የመሀል ተከላካይ አሌክስ ተሰማ ይጠቀሳል፡፡
የኢትዮጵያ የፀረ አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን በተለያዩ ተጫዋቾች ላይ ምርመራን ሲያደርግ ከቆየ በኋላ ተከላካዩ አሌክስ ተሰማ ላይ ፍንጭ መታየቱን ተከትሎ ጊዜያዊ ዕገዳን ከወራት በፊት መጣሉ ይታወቃል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ተጫዋቹ ካቲኖን የተባለ የተከለከለ ንጥረ ነገር ተጠቅሞ መገኘቱን ካረጋገጠ በኋላ በመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት አካሉ በኩል ቀደም ሲል ባስቻለው ችሎት ተጫዋቹ በጉዳዩ ላይ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑን እንዲሁም አበረታች ንጥረ ነገሩን ሆን ብሎ ወይም በቸልተኝነት ያልተጠቀመ መሆኑን ከግምት በማስገባት በማስጠንቀቂያ ቅጣት ብቻ እንዲታለፍ በማለት ወስኖ ነበር።
ሆኖም ውሳኔው ከጥፋቱ ጋር ተመጣጣኝ እና አስተማሪ አለመሆኑን ተከትሎ በጉዳዩ ላይ ይግባኝ የተጠየቀ በመሆኑ ይግባኝ ሰሚው አካል ጉዳዩን ሲመረምር እና ሲያከራክር ቆይቶ ሐምሌ 11 ዕለት በዋለው ችሎት የመጀመሪያ የዳኝነት አካሉ የወሰነውን ውሳኔ ሽሮ ተጫዋቹ ለአንድ ዓመት የሚቆይ ዕግድ እንዲጣልበት መወሰኑን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለሚዲያ አካላት በላከው ደብዳቤ ገልጿል።
በደብዳቤው ላይ እንደተጠቆመው አሌክስ ተሰማ የመጀመሪያው ዕግድ ከተጣለበት እ.ኤ.አ ከየካቲት 23 2022 ጀምሮ እስከ የካቲት 23 2023 ድረስ በማንኛውም ስፖርታዊ ውድድር ላይ እንዳይሳተፍ ዕግድ ተጥሎበታል። የመሀል ተከላካዩ አሌክስ ተሰማ ከመከላከያ ጋር ያለውን ውል ለተጨማሪ አንድ ዓመት ማራዘሙ ይታወሳል።