ወልቂጤ ከተማ ወደ ዝውውሩ ገብቷል

ወልቂጤ ከተማ የአራት ተጫዋቾችን ዝውውር ሲፈፅም የሁለት ነባር ተጫዋቾችን ውል አራዝሟል።

አሠልጣኝ ተመስገን ዳናን በኢትዮጵያ ቡና የተነጠቀው ወልቂጤ ከተማ ዘግየት ብሎም ቢሆን ወደ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ጎራ በማለት ስብስቡን እያጠናከረ ይገኛል። በዚህም ሁለት ተጫዋቾችን ለአንድ ዓመት ፣ ሁለት ተጫዋቾችን ደግሞ ለሁለት ዓመታት አስፈርሟል።

ቡድኑን የተቀላቀለው የመጀመሪያው ተጫዋች ሣለአምላክ ተገኘ ነው። በኢትዮጵያ ቡና የክለብ ህይወቱን የጀመረው ሣለአምላክ መጀመሪያ በውሰት ከዛም በቋሚነት በባህር ዳር ቤት አሳልፏል። የመስመር አማካይ እንዲሁም የመስመር ተከላካይ ሆኖ መጫወት የሚችለው ተጫዋቹም ከጣና ሞገዶቹ ጋር ከተለያየ በኋላ ወደ ሠራተኞቹ ቤት አምርቷል።

ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ አፈወርቅ ኃይሉ ነው። የቀድሞ የወልዋሎ ዓ/ዩ እና ሀዲያ ሆሳዕና ተጫዋች ባህር ዳር ከተማን ተቀላቅሎ የእግር ኳስ ህይወቱን እየቀጠለ ቢሆንም ጉዳት በዘንድሮ የውድድር ዓመት በታሰበው መልኩ እንዲጫወት አላደረገውም ነበር። አሁን ግን ዘለግ ላለ ጊዜ ከቆየበት ጉዳት አገግሞ ወደ ልምምድ የተመለሰ ሲሆን በቀጣይ ዓመትም ከቀድሞ የቡድን አጋሩ ጋር በወልቂጤ ለመጫወት ፊርማውን አኑሯል።

ወልቂጤን የተቀላቀለው ሦስተኛ ተጫዋች ያለፉትን ዓመታት በባህር ዳር ከተማ ቆይታ ያደረገው የመስመር አጥቂው ዜናው ፈረደው ሲሆን በወልቂጤ ከተማ የሚያቆየውን የሁለት ዓመት ውል ተፈራርሟል። አራተኛው የሰራተኞቹ ፈራሚ ደግሞ በነቀምት ከተማ እና ሀላባ ከተማ የተጫወተው እና ለተከታታይ ሁለት ዓመት ለአዲስ አበባ ከተማ የተጫወተው የመሐል ተከላካዮ ቴዎድሮስ ሀሙ ሲሆን ለሁለት ዓመታት ለወልቂጤ ከተማ ለመጫወት ፊርማውን አኑሯል።

ክለቡ ከዚህ በተጨማሪ የሁለት ተጫዋቾችን ውል አድሷል። በክትፎዎቹ ቤት ለተጨማሪ ዓመት ለመቆየት ውሉን ያራዘመው አንደኛው ተጫዋች ዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ ሲሆን ግዙፉ የግብ ዘብ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ ወዲህ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስኬታማ ዓመታትን አሳልፎ ወደ አዳማ ከተማ ካመራ በኋላ በያዝነው ዓመት የውድድር አጋማሽ ነበር ወልቂጤን በመቀላቀል የቻለው። ሌላኛው ውሉን ያራዘመው በዘንድሮ ዓመት ቡድኑን በመቀላቀል ጥሩ ግልጋሎት የሰጠው ጋናዊው ተከላካይ ዋሁቡ አዳምስ ለተጨማሪ ዓመት በክለቡ ይቆያል።

ያጋሩ