በአርባ ሁለት ክለቦች መካከል ሲደረግ የነበረው የክልል ክለቦች ሻምፒዮና በዛሬው ዕለት ሻኪሶ ከተማን ቻምፒዮን በማድረግ ተጠናቋል፡፡
በብሩክ ሐንቻቻ
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን አዘጋጅነት በሀዋሳ ከተማ ከሰኔ 27 ጀምሮ በአርባ ሁለት ክለቦች መካከል ሲከናወን የቆየዉ የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ዉድድር በዛሬው ዕለት በይፋ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ ቀደም ብሎ ውድድሩ ወደ አንደኛ ሊግ ያደጉ አስራ ስድስት ክለቦችን ከሳምንታት በፊት የለየ ሲሆን የዋንጫ ባለቤቱን የሚለየው ውድድር ግን ዛሬ ተከናውኗል፡፡ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ እና በሻኪሶ ከተማ መካከል የተደረገዉ የፍፃሜ ጨዋታም በሻኪሶ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።
በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ረፋድ 3 ሰዓት የተለያዩ ከፍተኛ አመራሮች እና የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ተወካዮች በተገኙበት የዋንጫው ጨዋታ ተካሂዷል፡፡ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ እና ሻኪሶ ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታም መደበኛዉ ክፍለ ጊዜ 1ለ1 በሆነ ዉጤት ተጠናቆ በተሰጠዉ የመለያ ምት ሻኪሶ ከተማ 2ለ1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የ2014 የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና አሸናፊ ሆኗል።
ከዋንጫ ጨዋታው በፊት በትላንትናው ዕለት በተደረገው የደረጃ ጨዋታ በደሌ ከተማ ዳባት ከተማን 3ለ2 በመርታት የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
ከዛሬው የፍፃሜ ጨዋታ በማስከተል ከአንድ እስከ ሦስት በመያዝ ላጠናቀቁት ሻኪሶ ከተማ የወርቅ ፣ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የብር እንዲሁም በደሌ ከተማ የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሲሆኑ የሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን ዉድድሩን በማዘጋጀቱ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።
በዉድድሩ ላይ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ፣ ባለሙያዎች እና ተቋማት የሰርተፍኬት ሽልማት ሲሰጣቸው የዉድድሩ የፀባይ ዋንጫን በደሌ ከተማ አግኝቷል።