የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የ25ኛ ሳምንት የዛሬ ጨዋታዎች ውሎ

ሊጠናቀቅ የአንድ ሳምንት ዕድሜ ብቻ በቀረው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የዛሬ ጨዋታዎች የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ድሬዳዋ ከተማ ፣ ጌዲኦ ዲላ እና አዳማ ከተማ ሲያሸንፍ አርባምንጭ ከተማ ከ አዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርተዋል፡፡

ድሬዳዋ ከተማ ቦሌን 1ለ0 ሲረታ አርባምንጭ ከተማ ከ አዲስ አበባ ከተማ ጋር ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል፡፡

በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ረፋድ 3 ሰዓት ላይ ድሬዳዋ ከተማ እና ቦሌ ክፍለከተማ ያደረጉት ጨዋታ ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ማራኪ የሆነ የሜዳ ላይ ፉክክርን አስመልክቶን በመጨረሻም በድሬዳዋ ከተማ አሸናፊነት ፍፃሜን አግኝቷል፡፡ ከእረፍት መልስ ከቀኝ መስመር በኩል በ60ኛው ደቂቃ ላይ ከቤተልሄም ታምሩ የተቀበለችውን ኳስ የቀድሞው የአርባምንጭ ከተማ አጥቂ ሰርካለም ባሳ የቦሌ ተከላካዮችን ስህተት ተጠቅማ በማስቆጠር ቡድኗ 1ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፎ እንዲወጣ አስችላለች፡፡

በተመሳሳይ ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሜዳ ላይ ይደረጋል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የአርባምንጭ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ ከተያዘለት ሰዓት ሁለት ሰዓታትን ያህል ዘግይቶ የሜዳ ለውጥ ተደርጎበት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ ተከውኗል፡፡ ብዙም ፉክክር እና ሙከራን ለማየት ያልታደልንበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ያለ ጎል 0ለ0 ተደምድሟል፡፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ጌዲኦ ዲላ ድል ቀንቷቸዋል፡፡

ከቀናት በፊት የሊጉ ቻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቅዱስ ጊዮርጊስ እጅጉን ተፈትኖ በመጨረሻም ድል ቀንቶታል፡፡ በተመልካቶች ከፍተኛ ድጋፍን ያገኘው ይህ ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ኳስን በመቆጣጠሩ ረገድ ተሽለው የቀረቡበት ቢሆንም ደካማ በነበረው የመከላከል ሂደታቸው በ30ኛ ደቂቃ ላይ በመዲና ዐወል አማካኝነት ጎል እንዲቆጠርባቸው አድርጓል፡፡

ከእረፍት መልስ ተመሳሳይ አጨዋወትን በሁለቱም በኩል ለማየት ያስተዋልን ቢሆንም በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ መጨረሻዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ያደረጉት እንቅስቃሴ ትኩረትን የሚስብ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ መዲና ዐወል ለራሷ እና ለቡድኗ ሁለተኛ ጎል ካስቆጠረች በኋላ ፍፁም በማጥቃቱ ረገድ የተዋጣላቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች እንደ ነበራቸው ብልጫ ወደ አቻነት የሚመጡ ቢመስሉም እየሩስ ወንድሙ ከተደጋጋሚ ሙከራ በኋላ ከሽንፈት ያላዳነች አንድ ግብ አስቆጥራ ጨዋታው በሊጉ ቻምፒዮን ንግድ ባንክ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በሌላኛው ሜዳ አቃቂ ቃሊቲ እና ጌዲኦ ዲላን ያገናኘው መርሐ-ግብር በጌዲኦ ዲላ 1ለ0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሆኗል፡፡ ከደመወዝ ክፍያ አለመፈፀም ጋር እየታገሉ ጨዋታቸውን ያደረጉት ጌዲኦ ዲላዎች አጥቂዋ ይታገሱ ተገኝወርቅ ያስቆጠረችው ብቸኛ ጎል ነች ባለ ድል ልታደርጋቸው የቻለችው፡፡

ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ ሲጋሩ አዳማ ከተማ በበኩሉ አሸንፏል፡፡

ፕሪምየር ሊጉን ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቁን ባረጋገጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ሊጉን እንደሚፈፅም ባወቀው ሀዋሳ ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ 1ለ1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡ የኢፌዴሪ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በስታዲየሙ ተገኝተው በተከታተሉት ጨዋታ 3ኛ ደቂቃ ላይ ቱሪስት ለማ አስደናቂ ጎል ከመረብ አሳርፋ ሀዋሳን መሪ ማድረግ ብትችልም ከዕረፍት መልስ 70ኛው ደቂቃ ላይ በሳጥን ውስጥ የሀዋሳ ተከላካይ ኳስን በእጅ ነክታለች በሚል የዕለቱ ዳኛ አስናቀች ገብሬ የሰጠችውን አወዛጋቢ የፍፁም ቅጣት ምት ንቦኝ የን ወደ ጎልነት ለውጣው ጨዋታው 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ፍፃሜን አግኝቷል፡፡

አዳማ ከተማ በበኩሉ ባህርዳር ከተማ ላይ ድል የተቀናጀበትን ውጤት ማስመዝገብ ችሏል፡፡ የቀድሞው የደደቢት የአማካይ እና የመስመር ተጫዋች ትዕግስት ዘውዴ ያስቆጠረቻቸው ሁለት ጎሎች አዳማን 2ለ0 አሸናፊ መሆን እንዲችል አድርጋለች፡፡

ያጋሩ