ከትናንት በስትያ ለመከላከያ ለመጫወት ፊርማውን ያኖረው የአምሳሉ ጥላሁን የዝውውር ጉዳይ አዳዲስ ነገሮች እየተሰሙበት ነው።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዝውውር መስኮት ከሁለት ሳምንታት በፊት የተከፈተ ሲሆን በርካታ ክለቦችም አዳዲስ ተጫዋቾችም ወደ ስብስባቸው እየቀላቀሉ ይገኛሉ። በመስኮቱ ንቁ ተሳትፎ ከሚያደርጉ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው መከላከያም ከትናንት በስትያ አምሳሉ ጥላሁንን የግሉ አድርጎ የነበረ ሲሆን ዝውውሩ ይፋ ከሆነ በኋላ ግን ተጫዋቹ ላይ የተለያዩ ሀሳቦች እየተነሱ ይገኛሉ።
ተጫዋቹ ጦሩን ለሁለት ዓመት መቀላቀሉን በፎቶ ማስረጃ አስደግፈን ዘገባ ሰርተን የነበረ ቢሆንም በቀጣዩ ዓመት ከቀድሞ ክለቡ ፋሲል ከነማ ጋር ሊቀጥል የሚችልበት ዕድል እንዳለ ለማወቅ ችለናል። የፋሲል ከነማ አመራሮች ተጫዋቹ በመከላከያ ለመጫወት ከፈረመ በኋላ አግኝተውት ሀሳብ እንዲቀይር እና ለስድስት ዓመታት ግልጋሎት በሰጠበት ክለብ እንዲቀጥል እንዳሳመኑት ሰምተናል።
ተጫዋቹ ለመከላከያ ህጋዊ በሆነ መንገድ ፊርማውን አኑሮ የነበረ በመሆኑ ከመከላከያ ጋር ያለውን ውል በስምምነት ካልቀደደ በቀር ከፋሲል ጋር ለመጫወት በድጋሜ ከፈረመ በእግር ኳሱ የበላይ አካል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቅጣት የሚጠብቀው ሲሆን ከመከላከያ ጋር ያለውን ውል ለመቅደድም ንግግር ላይ እንዳለ ሶከር ኢትዮጵያ ለማወቅ ችላለች። ምናልባትም ነገ ተጫዋቹ አጣብቂኝ የገባበት ጉዳይ ሊፈታ እንደሚችል የሰማን ሲሆን ቀጣይ ክለቡም ይረጋገጣል ተብሎ ይጠበቃል።