የተጫዋቾችን ጤና እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል ?

ወቅቱ ክለቦች አዳዲስ ተጫዋቾችን እያስፈረሙ የሚገኙበት እንደመሆኑ የተጫዋቾችን ጤንነት በተመለከተ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ነጥቦችን በዚህ ፅሁፍ አንስተናል።

የ2014 የውድድር ዘመን መጠናቀቅን ተከትሎ ክለቦች በስፋት በዝውውር መስኮት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ዝውውሮች ግን ምን ያህል በህክምና ምርመራ የተደገፉ እና የተጫዋቾቹን ጤንነት ግምት ውስጥ ያስገቡ ናቸው የሚለው ጉዳይ ጥያቄን ያስነሳል፡፡

በፕሮፌሽናል ደረጃ አንድ ተጫዋች ለክለብ በሚፈርምበት ወቅት የጤና ምርመራ እንደሚደረግለት ይታወቃል፡፡ ይህ ምርመራ ተጫዋቹ ያለበትን የጤና ሁኔታ ከማረጋገጡ በተጨማሪ ማንኛውም ዓይነት ህመም ወይም ጉዳት ካለበት ለመለየት ያስችላል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የእግር ዖኳስ ተጫዋቾች በድንገተኛ የልብ ድካም እና መሰል ህመሞች ህይወታቸው ሲያልፍ ተመልክተናል፡፡ እንደዚህ ያሉ ችግሮች እንዳያጋጥሙ ቅድመ ምርመራ አስፈላጊ ነው፡፡

በሚደረገው ምርመራ ወቅት የግል ሆነ የቤተሰብ የህክምና ታሪክ የሚመዘገብ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ደም ግፊትን መለካት እና የልብ ኤሌክትሪካዊ መስተጋብር የሚለካው ማሽን (ECG) ተግባር ላይ ይውላል፡፡ ለምሳሌ ያህል ምክንያቱ ያልታወቀ ራስን መሳት ፣ የልብ ምት ለራስ እስኪታወቅ ድረስ መጨመር (palpitation) ፣ የደረት ህመም ወይንም በእንቅስቃሴ ጊዜ የሚፈጠር የትንፋሽ ማጠር በህክምና ታሪክ ወቅት ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዘር ያለ የልብ ህመም ተለይቶ መታወቅ አለበት፡፡ እነዚህን መሰረት በማደረግ የተለያዩ ምርመራዎች ይታዘዛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የልብ አልትራሳውንድ አንዱ ነው፡፡ በእንቅስቃሴ የሚሰራ stress test ደግሞ ልብ ውስጥ ያለ የደም ዝውውር ትክክል መሆን እና አለመሆኑን ይነግረናል፡፡

ለከፍተኛ ህመም ከሚዳርጉት የልብ እና የአተነፋፈስ ዕክሎች በተጨማሪ የአጥንት እና የጡንቻ ጉዳት አስቀድመው መለየት አለባቸው፡፡ እነዚህ ምርመራዎች አሁን ያሉ ችግሮችን ለማወቅ ብቻ ሳይሆን ወደፊት ምን ዓይነት ጉዳቶች ሊደርሱ ይችላሉ የሚለው ጉዳይ መታወቅ እንዲችል ይረዳሉ፡፡ እነዚህ ምርመራዎች የሚካሄዱት የተጫዋችን ታሪክ በመውሰድ እና አካላዊ ምርመራ በማደረግ ሲሆን አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ እንደ x-ray, MRI, CT Scan ሊታዘዙ ይችላሉ፡፡

የጉልበት እና የቁርጭምጭት ጉዳቶች በተለየ ትኩረት የሚቃኙ ነገሮች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ደግሞ በልስልስ አጥንት ( cartilage) እና በመገጣጠሚያ ዙሪያ ከበድ ያሉ ጉዳቶች እንዲከሰቱ ስለሚያደርጉ ነው፡፡ እግርኳስ በተለምዶ stop-and-go sport ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም የተባለበት ምክንያት መሮጥን፤ መቆምን እና አቅጣጫ መቀየርን በአንድ ላይ አቅፎ በመያዙ አማካኝነት ነው፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ መጋጣጠሚያ ላይ የሚኖረው ጫና ከፍ ያለ ነው፡፡ ስለዚህ ተጫዋቾች እንደዚህ ላለው ኃይልን ለሚፈልግ ስራ ብቁ መሆናቸው መረጋገጥ አለበት፡፡

የጭንቅላት ጉዳት እና ከዛ ጋርም ተያይዞ አንጎል ላይ የሚደርሱ ህመሞች የተጫዋች ታሪክ በሚመዘገብበት ወቅት ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል ይካተታሉ፡፡ ተደጋጋሚ የሆኑ ግጭቶች የአንጎል ስራ ላይ ከፍተኛ ጫናን ያሳድራሉ፡፡ ስለዚህ በተደጋጋሚ እንደዚህ ዓይነት ጉዳቶች ያጋጠሙት ተጫዋችን ከማስፈረም በፊት ክለቦች ከፍተኛ የሆነ እና ጥንቃቄ የተሞላበት ምርመራ ማድረግ አለባቸው፡፡

የጡንቻ ጉዳቶች በሰፊው የሚስተዋሉ እና በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ ናቸው፡፡ የተጎዳው ጡንቻን ትኩረት ያደረገ ልምምድ የማገገሚያ ጊዜው አጭር እንዲሆን ያስችላል፡፡ የጤና ምርመራ ታሪክ በሚወሰድበት ወቅት እንደ ትልቁ የእግር አጥንት እና በተለምዶ Achilles tendon ተብለው የሚጠሩት ጅማቶች ላይ ትኩረት ይደረጋል፡፡ ለግብ ጠባቂ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ትኩረቱ ጣት ላይ ይሆናል፡፡

ከላይ የጠቀስናቸው ምርመራዎች በሀገራችን ክለቦች በምን ያህል ደረጃ እየተተገበሩ ነው የሚለው ጉዳይ አሁንም አጠያያቂ ነው፡፡ በተለይ አሁን የምንገኝበት ወቅት የዝውውር ከመሆኑ አንፃር ክለቦች ተጫዋቾችን በሚያስፈርሙበት ወቅት ምን ያህል ጥንቃቄ እና ምርመራ ያደርጋሉ የሚለው ጉዳይ ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡ ሆኖም በከፍተኛ በጀት እየፈሰሰበት ባለው እግርኳሳችን ውስጥ ክለቦች ገንዘባቸውን ብቁ የሆነ ተጫዋች ላይ ስለማዋላቸው ተጫዋቾችም ያሉበትን ወቅታዊ የጤንነት ሁኔታ ከማወቅ አንፃር ጉዳዩ ከፍ ያለ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ ዕሙን ነው።